ለጋምቤላ ክልል ልማት ስኬታማነት የአመራር አካላት ድጋፍና ክትትል ሊጠናከር እንደሚገባ አፈ ጉባዔው አስገነዘቡ

70

ጋምቤላ ጥር 28/2011 ለክልሉ ልማት፣መልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ስኬት የአመራር አካላት ድጋፍና ክትትል ሊጠናከር እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አስገነዘቡ፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አራተኛ የስራ ዘመን ስምንተኛ መደበኛ ጉባዔ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ላክዳር ላክባክ ጉባዔውን ሲከፍቱ እንዳሳሰቡት በክልሉ የተጀመረውን የልማት፣የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ስኬት የአመራር አካላት ድጋፍና ክትትል ሊጎለብት ይገባዋል።

የምክር ቤት አባላት ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች በመፍታት የወጣቱንና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሰሩም  ጠይቀዋል።

ምክር ቤቶች የሃሳብ ልዩነቶች በአግባቡ የሚስተናገዱበትን ዕድል በመፍጠር የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡

ወጣቱ ከግጭት ምንም ዓይነት ትርፍ እንደማይገኝ በመገንዘብ እንደ ክልልም ሆነ እንደ አገር የተጀመረውን ለውጥ እውን ለማድረግ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም አሳስበዋል።

የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ ምክር ቤት እየሰራ  መሆኑን የጠቆሙት አቶ ላክዳር፣ የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ለማጠናከር የዴሞክራሲ ተቋማት ተቀናጅተው የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።

ጉባዔው በሁለት ቀናት ቆይታው የክልሉን የ2011 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የኦዲት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን አድምጦ ተወያይቶ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

በተያያዘ የበጀት ዓመት የቀጣይ ስድስት ወራት የተከለሰ ዕቅድ፣ረቂቅ ዓዋጆችንና ሹመቶችን መርምሮ ያጸድቃል፡፡

በጉባዔው የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ከ300 በላይ የክልል፣የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣የሴቶችና የወጣቶች አደረጃጀቶች እንዲሁም የህጻናት ፓርላማ አባላት ተሳትፈዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም