ለአምባሳደሮች ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላት ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንዲያድግ እንዲሰሩ ተልዕኮ ተሰጠ

113

 አዲስ አበባ ጥር 28/2011 ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንዲያመራ የሁሉም አምባሳደሮች ተልዕኮ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ አዲስ ለተመደቡ ሃያ አምባሳደሮች የአስር ቀን ስልጠና እየሰጠ ነው።

አምባሳደሮቹ ላለፉት ሰባት ቀናት በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና በዘርፉ ልምድ ባካበቱ አምባሳደሮች ሲሰለጥኑ የቆዩ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ "የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዲፕሎማሲና ዲፕሎማቶች " በሚል ርዕስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ስልጠና ሰጥተዋል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንዲፈጠር በየአገሮቹ የተመደቡ አምባሳደሮች ተልዕኮ ነው።

እንዲሁም በአገር ደረጃ ትኩረት ለሚደረግበት ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ትስስር አምባሳደሮቹ የሚጠበቅባቸውን ውጤት እንዲያስመዘግቡ በሚኒስቴሩ የሚሰጠው ስልጠና ትልቅ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ያላት ተሳትፎና ግንኙነት በሌሎች የዓለም አገሮች ለሚኖራት ማንኛውም እንቅስቃሴ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንዳለው ያብራሩት ቃል አቀባዩ የአገሪቱን ሁለንተናዊ ግንኝነት ለማጠናከር ለአምባሳደሮቹ የሚሰጠው ስልጠና አንድ አካል ተደርጎ ተወስዷል ብለዋል።

በሁሉም ሚሲዮኖች የሚመደቡ አምባሳደሮች ኢትዮጵያ ከአገሮቹ ጋር በሚኖራትን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ላይ ተገቢውን ግንዛቤ ይዘው እንዲሰማሩ የሚደረግ መሆኑን አቶ ነቢያት ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላት እንቅስቃሴ በኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ትልቅ ውጤት እያስመዘገበች ሲሆን በተለይ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ''ወደ ኢኮኖሚ ውህደትና ክልላዊ ትስስር'' ለማሳደግ ትልቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአምባሳደሮቹ ስልጠና ከሦስት ቀን በኋላ የሚጠናቀቅ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ዛሬ ከሰጡት ስልጠና በተጨማሪ ቀጣይም የሥራ አቅጣጫዎችን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ኢትጵያን ወክለው የሚሰሩባቸውን አገሮች ታህሳስ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ይፋ ሲያደርግ እንዳስታወቀው አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድ በጂቡቲ፣ ወይዘሮ አለምፀሐይ መሠረት ኡጋንዳ፣ አቶ ተፈሪ ታደሰ ደቡብ ሱዳን እና አቶ መለስ አለም ኬንያ በአምባሳደርነት እንዲሰሩ ተመድበዋል።

ኢትዮጵያ ከቀጣናው አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በኢኮኖሚ እንዲተሳሰር ለማስቻል ወደብ በጋራ ማልማትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሷ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም