የራያ አዘቦ ወረዳ አርሶ አደሮች የገበያ ትሰስር ባለመፈጠሩ ለምርታችን ተገቢውን ዋጋ አላገኘንም አሉ

84

ማይጨው ጥር 28/2011 በትግራይ ደቡባዊ ዞን በራያ አዘቦ ወረዳ በመስኖ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ገለጹ።

ከአርሶ አደሮቹ አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስረዱት በመስኖ ለሚያለሙት ምርት የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ በምርታቸው ተጠቃሚ  አልሆኑም።

በራያ አዘቦ ወረዳ የካራዓዲሻቦ ቀበሌው አርሶ አደር የማነ ሃፍተ በዓመት ሁለት ጊዜ በመስኖ ከሚያለሙት መሬት አትክልትና ፍራፍሬ ቢያመርቱም፤ በገበያ እጦት ምክንያት የምርቱ ተጠቃሚዎች እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

ሌላው የዚሁ ወረዳ  አርሶ አደር የሆኑት አቶ ተስፋይ መረሳ በበኩላቸው በየዓመቱ በመስኖ ከሚያለሙት የጓሮ አትክልት እስከ 50 ኩንታል ምርት የሚሰበስቡ ቢሆንም፤የገበያ  ትስስር ባለመፈጠሩ ከሚሸጠው የሚበላሸው እንደሚበልጥ ተናግረዋል።

ከምርቱ የሚያገኙት ገቢ ለሥራው ከሚያወጡት ወጪ ጋር ባለመጣጣሙ ለኪሳራ መዳረጋቸውን አስረድተዋል።

"ለወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ችግራችንን በተደጋጋሚ ጊዜ ብናሳውቅም፤ የሚመለከተው አካል እስካሁን ችግራችንን አልፈታልንም" ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

አቻምና የመስኖ ሥራ መጀመሩን የሚናገረው ወጣት ገዛኢ ገብረ ሚካኤል በገበያ አቅርቦት ችግር በሚያለማው በርበሬና የጓሮ እትክልት ተጠቃሚ  አለመሆኑን ተናግሯል።

ወደ አካባቢው የሚመጡ ደላሎች ለአርሶ አደሩ የሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ  ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑን አስረድቷል።

በራያ አዘቦ ወረዳ ግብርና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት የመስኖ ልማት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ኪሮስ ተጠይቀው በነጋዴ፣በደላላና በአርሶ አደሩ መካከል ያለው ያልተገባ የግብይት ግንኙነት በገበያ ትስስር ረገድ ችግር መፍጠሩን አስረድተዋል።

ችግሩን ለማቃለል የአካባቢው አርሶ አደር የጓሮ አትክልትን በአንድ ጊዜና በብዛት ከማልማት ይልቅ፤ በዓይነትና በተለያዩ ጊዜያት እያፈራረቀ እንዲያመርት መክረዋል።

የትግራይ ደቡባዊ ዞን የመስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ አሰፋ አስረስ በበኩላቸው የአርሶ አደሮቹን የገበያ ችግር ለመፍታት ከክልሉ የግብርና ምርት ሽግግርና ግብይት ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በመቀሌ ከተማ ከሚገኙ የጅምላ ነጋዴዎች ጋር በመነጋገር የአርሶ አደሮቹን ምርት በቀጥታ በመግዛት ችግሩን ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም