መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱን ቱሪዝም ልማት በማሳደግ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

67

ደብረ ማርቆስ ጥር 28/2011 መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱን ቱሪዝም ልማት ለማሳደግ ባህላዊና ተፈጥሯዊ እሴቶች በመጠበቅና በማስተዋወቅ ሚናቸውን እንዲወጡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጠየቀ።

ሚኒስቴሩ በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ የቱሪስት መስህቦችን ለመገናኛ ብዙኃን አካላት ለማስተዋወቅ ከጥር 18/2011 ጀምሮ የተካሄደው ጉብኝት ትናንት ተጠናቋል።

የሚኒስቴሩ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ ገዛኽኝ አባተ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱ የቱሪዝም ልማትን ለማሳደግ የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባቸዋል።

የአገሪቱ ባህላዊ፣ተፈጥሮአዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች በተገቢው መንገድ ባለመተዋወቃቸው ዘርፉ በሚጠበቀው ልክ እንዳላደገም ተናግረዋል።

የቱሪስት መስህቦችን ለአገር ውስጥና ለውጭ ቱሪስቶች ለማስተዋወቅ በአገር አቀፍ ደረጃ የባህልና ቱሪዝም የሚዲያ ፎረም መቋቋሙን አመልክተዋል።

ጉብኝቱ የአካባቢው ባህላዊና ተፈጥሮአዊ እሴቶች እንዲተዋወቁ፣ እንዲለሙና ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፉ እንዲሁም የቱሪስት ፍሰትን በማሳደግ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እንደሚያስችል አቶ ገዛኸኝ አስረድተዋል።

የሚዲያ ፎረሙ አስተባባሪ አቶ ዘሪሁን ግርማ በበኩላቸው አሁን ባለው አሰራር ፎረሙ የአገሪቱን የቱሪዝም ሀብት ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑንና ፎረሙ ከተቋቋመ በኋላም ለዘርፉ የሚሰጠው የመገናኛ ብዘኃን ሽፋን መሻሻል እንደታየበት ተናግረዋል።

ለወደፊትም በቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ ጋዜጠኞች ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የኢ ቢ ኤስ ሪፖርተር ፍስሀ ደሳለኝ ጉብኝቱ በአካባቢው ያለውን የቱሪዝም ሀብት ለማየት እንዳስቻለው ገልጾ፣ይህንኑ ለተመልካቾች በማስተዋወቅ ሙያዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጿል።

የዳሽን ሚዲያ ኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘመነ ይዋኒስ በበኩላቸው ጉብኝቱ የአካባቢው ማህበረሰብ እንግዳ አቀባበል ባህሉን ያልረሳና ያልለቀቀ ሆኖ በማግኘቴ ተደስቻለሁ ብለዋል።

የአካባቢውን መስህቦችን ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩም ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

በጉብኝቱ ከ20 መገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተውጣጡ ጋዜጠኞችና የባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም