ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ላለባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አርአያ ነው- አፈ ጉባዔ ኬሪያ ኢብራሂም

90

ጂንካ ጥር 27/2011 በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ሌሎች ግጭት ላለባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አርአያ እንደሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ገለፁ።

በዞኑ ያለው ሰላምና መረጋጋት በተምሳሌትነት የሚጠቀስ መሆኑን አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ተናግረዋል።

በደቡብ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ የሚገኙ 16 ብሄረሰቦች የተሳተፉበት የባህል ፌስቲቫል ዛሬ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል።

ፌስቲቫሉ በዞኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን "ባህላዊ እሴቶች ለአብሮነትና ለልማት" በሚል መሪ ቃል ነው የተካሄደው።

አፈ ጉባዔዋ በፌስቲቫሉ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ያለው ሰላምና መረጋጋት ለመማር ማስተማር ስራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ በመሆኑ ለሌሎች ግጭት ላለባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አርአያ ነው።

በርካታ ብሄረሰቦች የሚኖሩበት ዞኑ በአካባቢው ያለው ሰላምና መረጋጋት በአገር አቀፍ ደረጃ በተምሳሌትነት የሚጠቀስ ነውም ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የተካሄደው ፌስቲቫል በዞኑ ያለውን ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ለማስተዋወቅ የሚረዳ መልካም ተግባር እንደሆነም ተናግረዋል።

እንዲሁም የዞኑን ባህልና እሴቶች ለሌሎች አካላት ለማሳወቅ የጀመራቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን አንስተዋል። 

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉት፤ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ አካባቢያዊ ጥናትና ምርምሮች ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆኑ አገር በቀል እውቀትን ለተማሪዎችና ለኀብረተሰቡ ለማሳወቅ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ የጀመረው ጥናትና ምርምር ያለው ፋይዳ የጎላ ነው።

ዩኒቨርስቲው በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመደገፍ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ለሚማሩ ተማሪዎች በኮምፒዩተር አማካይነት የሚሰጠውን መጽሕፍ አቅርቦት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል። 

ዩኒቨርሲቲው በዞኑ ባህልና እሴቶች ላይ ለሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች የልህቀት ማዕከል በመሆን ማገልገል እንዳለበት ፕሮፌሰር አፈወርቅ  ጠቁመዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ገብሬ ይምቲሶ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ብሄረሰቦች የሚያስተዋውቅ ፌስቲቫል ባለመካሄዱ የብሔረሰቦቹን ባህልና እሴት በማስተዋወቅ ረገድ የሚፈለገው ያህል አልተሰራም ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ማህረሰባዊ አገልግሎት ለኀብረተሰቡ አለመስጠቱን ተናግረዋል።

ዘንድሮ የባህል ፌስቲቫሉ ለመጀመሪያ ጊዜ መዘጋጀቱ 16ቱ ብሔረሰቦች እርስ በርስ እንዲተዋወቁና የባህል ልውውጥ እንዲያደርጉ ምቹ አጋጣሚ የፈጠረ በመሆኑ ወደፊት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚካሄድም አመልክተዋል።   

የፌስቲቫሉ ዓላማ በዞኑ የሚገኙ ብሔረሰቦችን ከማቀራረብ ባሻገር ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የ16ቱን ብሔረሰቦች ቋንቋ፣ ባህልና እሴት እንዲያውቁ ማድረግ እንደሆነም ገልጸዋል።

እንዲሁም በዞኑ ግጭቶች ሳይከሰቱ የአገር አንድነትና ሰላም ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ፕሮፌሰር ገብሬ አስረድተዋል።  

በፌስቲቫሉ የዞኑ ብሔረሰቦች የምግብ፣ የሙዚቃና የዕደ-ጥበብ ስራዎች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን በባህል ብዝሃነት የሚታወቅና በበርካታ የውጭ አገር ዜጎች የሚጎበኝ አካባቢ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም