ኮሌጆቹ የአገር ውስጥ ምርቶችን ጥራትና ዲዛይን ለማሻሻል ትኩረት መስጠት አለባቸው

148

አዳማ ጥር 27/2011የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች ገቢ ሸቀጦችን በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የቴክኖሎጂ ጥራትና ዲዛይን ትኩረት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው የኦሮሚያ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ አሳሰበ።

ቢሮው ባለፉት ስድስት ወራት በዘርፉ ያከናወናቸውን ስራዎች  ከሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር  ዛሬ በአዳማ ከተማ መገምገም ጀምሯል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ኤባ ገርባ በግምገማው መክፈቻ ላይ እንዳሳሰቡት  ኮሌጆቹ ገቢ ሸቀጦችን በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ጥራትና ዲዛይንን ለማሻሻል መሥራት አለባቸው።

ኮሌጆቹ በቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ አበረታች ውጤቶች እያሳዩ ቢሆንም፤በጥራትና ዲዛይንን አሻሽሎ ለተጠቃሚዎች በማድረስ በኩል ያለውን ክፍተት መሙላት ያስፈልጋል ብለዋል።

በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪና በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችም ክፍተቱን በሚሞሉ መልኩ ለማውጣትና የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢንዱስትሪ ኤክስቴሽን አገልግሎት በተሟላ መልኩ ለማህበራትና አንቀሳቃሾች እየተሰጠ እንዳልሆነ በኮሌጆችና በማስልጠኛ ተቋማት ባደረጉት ግምገማና ክትትል ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በምርምር የሚወጡ ቴክኖሎጂዎችም ቢሆኑ በጥራትና ዲዛይን ላይ ክፍተት እንደሚታይባቸውና ለተጠቃሚዎች በሚፈለገው መልኩ ደርሰው ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮቹን በሚፈቱበት ደረጃ ላይ እንዳልሆኑ አቶ ኤባ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት ኮሌጆችንና የማሰልጠኛ ተቋማትን በሰው ኃይል የማብቃት ፣ በግብዓቶች ፣ በቤተ ሙከራዎችና በወርክሾፖች የማደራጀት፣ የአሰልጣኞችን እውቀት፣ክህሎትና አቅማቸውን እያጠናከረ ነው ብለዋል።

የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ በክልሉ እየተገነቡ ያሉትን የኢኮኖሚ ልማት መዋቅር በእውቀትና ቴክኖሎጂ የሚደግፍ የሰው ኃይል ለማውጣት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቢሮው የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ግርማ ረጋሳ በበኩላቸው በተቋማቱ የሚታየውን የአቅምና የቴክኖሎጂ ክፍተት ለመሙላት የገበያ አዋጭነት ጥናት መከናወኑን አስረድተዋል።

በዘርፉ የተሻለ ውጤት ካመጡት የውጭ አገሮች ጋር ትስስር በመፍጠር በቴክኖሎጂ ሽግግርና ማላመድ ላይ በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ 176 የቴኪኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆችን በግብዓት፣በላቦራቶሪና ወርክሾፖች መደራጀታቸውን አስረድተዋል።

አሰልጣኞች ያለባቸውን የእውቀትና ክህሎት ችግር ለማቃለል ከ24 የፖሊ ቴኪኒክ ኮሌጆች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ከ600 በላይ ቴክኖሎጂዎች በተቋማቱ በምርምር መውጣታቸውን ጠቅሰዋል።

በግምገማ መድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የአትሌት ቀነኒሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ ነስረዲን ቃዲ በቴክኖሎጂ ፈጠራ ፣ ጥራትና ዲዛይን ማሻሻያ ፣ የገበያ ፍላጎትና አዋጭነት ጥናት ፣ ማኑፋክቸሪንግ ፣ የኢንዱስትሪ ኤክስቴሽን አገልግሎት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው የግምገማ መድረክ ላይ ከክልሉ 20 ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም