አፍሪካውያንን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን መወጣት አለባት ተባለ

107

አዲስ አበባ ጥር 27/2011 አፍሪካውያንን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን መወጣት እንደሚገባት የአፍሪካ ስነ-ፈለክና ስፔስ ሳይንስ ኢንሼቲቭ (African Initiative for Planetary and Space sciences) ገለጸ። 

የመጀመሪያው የአፍሪካ ስነ-ፈለክና ስፔስ ሳይንስ ኢንሼቲቭ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት ዓመታዊ ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

በቤልጂዬም የአንትወርፕ ዩኒቨርሲቲ የአስትሮፊሲስትና የአፍሪካ ስነ-ፈለክና ስፔስ ሳይንስ ኢንሼቲቭ ተወካይ ፕሮፌሰር ካትሪን ኮሌንበርግ እንዳሉት፤ የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አገሮች ተቀራርበው ችግራቸውን በጋራ እንዲፈቱ ያግዛል።

ኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ ፖሊሲ አወጥታ በተሻለ ፍጥነት የምትንቀሳቀስ በመሆኗ ለአፍሪካ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት የመሪነት ሚናዋን መወጣት አለባት ብለዋል።

አፍሪካውያን በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ በዓለም ታዋቂና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉት በቅንጅት መስራት ሲችሉ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

ለዚህ ደግሞ የእስር በርስ የልምድ ልውውጥ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ፕሮፌሰር ካትሪን፤ ኢትዮጵያም ልምዷን በማካፈል ቀዳሚ መሆን ይኖርባታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለስፔስ ሳይንስ ተመራማሪዎች ቀዳሚ ስትራቴጂያዊ አገር በመሆኗ አህጉራዊ የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉባዔዎች በአዲስ አበባ እንዲዘጋጁ መደረጉን ገልጸዋል።

እርስ በርስ የሚደረግ የልምድ ልውውጥ የተሻለችና በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተሳሰረች አፍሪካን ለመፍጠር እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

የመጀመሪያው የአፍሪካ ስነ-ፈለክና ስፔስ ሳይንስ ኢንሼቲቭ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄዱ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ የስፔስ ሳይንስ ዕድገት የመጀመሪያውን ፍኖተ ካርታ ማስቀመጥ ይሆናልም ብለዋል።

አፍሪካውያንን በስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር በሚደረገው እንቅስቃሴም የአፍሪካ ስነ-ፈለክና ስፔስ ሳይንስ ኢንሼቲቭ አስፈላጊውን የቴክኒክ፣ የሙያና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ፕሮፌሰር ካትሪን አረጋግጠዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሹመቴ ግዛው እንዳሉት አፍሪካን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የስፔስ ሳይንስና የቴክኖሎጂ ዘርፍን ለማሳደግ ዘግይተው የጀመሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ያለውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም አለባቸው።

ኢትዮጵያ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ አደረጃጀቶችና ተቋማዊ አሰራሮችን በቁርጠኝነት ተግራዊ እያደረገች መሆኗን አንሰተዋል።

አፍሪካውያን በስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የዳበረና ጠንካራ ትስስር ያላት አህጉር ለመፍጠር ያለውን ህልም እውን ለማድረግ በዘርፉ አቅም ካዳበሩ አገሮች ጋር ያለውን ልምድ አጣጥሞ ለመስራት ጥረት ይደረጋል ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች በዘርፉ ከዳበሩ አገሮች ልምድ በመውሰድ በአየር ንብረት፣ በውሃና በመሬት ያሏትን ሀብቶች ጥቅም ላይ ለማዋል እንደምትሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም