የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለልማት ተነሺዎች የፈጸመው የካሳ ክፍያ መመሪያ የጣሰ ነው ተባለ

103

አዲስ አበባ  ጥር 27/2011 የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለልማት ተነሺዎች የፈጸመው የካሳ ክፍያ የአሰራር መመሪያን የጣሰ መሆኑን የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ለግንባታው ፍጥነት ሲባል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ መመሪያ የጣሰ ክፍያ እንደሚፈጸም አረጋግጠዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር የ11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች የግንባታ ክዋኔ ኦዲት ግኝትን ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።

ሚኒስቴሩ ለ468 ባለ ይዞታዎች የካሳ ክፍያ በግል አካውንታቸው ገቢ በማድረግ የካሳ ክፍያውን መፈጸም ሲገባው በደደቢት አነስተኛ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ እና በክልሎች የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በኩል ከ79 ሚሊዮን ብር በላይ በጥቅል ወደ አካውንታቸው እንዲገባ አድርጓል።

ይህ ደግሞ ሚኒስቴሩ ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም ያወጣውን የአሰራር መመሪያ የጣሰና ተገቢው ክፍያ ለተገቢው ባለይዞታ መከፈሉን ያላረጋገጠ መሆኑ ተገልጿል።

ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ ለተነሺዎች የከፈለው የካሳ  ክፍያ በእቅድ፣ በህግና በመመሪያ ያልተመራ ነው።

በጥቅል የተከፈለው የካሳ ክፍያ ለባለይዞታዎቹ በአግባቡ መድረስ አለመድረሱ የሚረጋገጥበት መንገድ አለመኖሩን ጠቁመዋል።

ለራያ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ የልማት ተነሺዎች በደደቢት ብድርና ቁጠባ ሒሳብ ቁጥር፣ ለሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ በፍቼ ማዘጋጃ ቤትና አገልግሎት መምሪያ፣ ለቦንጋና ለእንጅባራ ዩኒቨርሲቲዎች በዞንና ከተማ አስተዳደር ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ በኩል ጥቅል ሒሳብ ገቢ መደረጉ በክዋኔ ኦዲት መረጋገጡን ገልጸዋል።

በዚህም ገንዘቡ ለካሳ ተከፋዮቹ መድረስ አለመድረሱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለመገኘቱን አቶ ገመቹ ተናግረዋል።

የካሳ ክፍያው በበቂ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ በመሆኑ በደምቢ ዶሎ፣ ወራቤ፣ ራያ፣ መቅደላ አምባ እና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች በእቅድ ከተያዘው 100 ሚሊዮን ብር በጀት በላይ 215 ሚሊዮን ብር ክፍያ እንደተፈጸመ በክዋኔ ኦዲቱ የተደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል።

አሰራሩ መንግስትን አላስፈላጊ ለሆነ ወጪ ከመዳረጉም ባለፈ የተከፈሉ የካሳ ክፍያ ማስረጃዎች ጥራት መጉደል፣ በአንድ አካውንት ሁለት ጊዜ ክፍያ መፈጸም፣ የባንክ አካውንትን በእስኪሪቢቶ ሰርዞ መክፈልና ባለይዞታዎች የካሳ ግምቱ ትክክለኛ ስለመሆኑ በፊርማ ሳያረጋግጡ መክፈልን የታዩ ችግሮች መሆናቸውን አመልክተዋል።

ለአብነትም በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ ያለማስረጃ ሰነድ መከፈሉን ዋና ኦዲተሩ ጠቁመው አሰራሩ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ ያለውን አመኔታ የሚቀንስ ድርጊት መሆኑን ተናግረዋል።

በገንዘብ ሚኒስቴር የማህበራዊ መስሪያ ቤት ኦዲት ቡድን መሪ አቶ አባተ ከበደ ''ለጊዜያዊ ችግር መፍትሄ የመንግስትን መመሪያ መጣስ አግባብነት የለውም'' ብለዋል።

ተቋሙም የሚታዩ የአሰራር ግድፈቶች በአስቸኳይ ሊታረሙ የሚገባቸውና ባለፉት 13 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ የታዩ ግድፈቶች ሊታረሙ የሚገባቸው አሰራሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት የካሳ ክፍያ የሚፈፀመው የዞኑ አስተዳደር ለክልሉ በሚሰጠው መረጃ መሆኑንና ክፍያው የማይገባቸውና ማስረጃ የሌላቸው ሰዎች ''ወራሾች ናቸው የባንክ ደብተር የላቸውም'' በሚል ሰበብ ክፍያ እንደሚፈጸም ተናግረዋል።

ለግንባታው ፍጥነት ሲባል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ መመሪያ የጣሰ ክፍያ መፈጸሙንም አምነዋል።

ክፍያው በአግባቡ ለልማት ተነሺዎች መድረሱን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጣርቶ የተሟላ መረጃ ለቋሚ ኮሚቴውና ለዋና ኦዲተር እንደሚያቀርብም ዶክተር ሳሙኤል አረጋግጠዋል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መሐመድ የሱፍ  በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ለልማት ተነሺዎች ተብሎ ወደ ሌላ የሂሳብ ደብተር የገባው ገንዘብ ለባለ ይዞታዎች መድረሱን የሚያረጋግጥ መረጃ እንዲያቀረብ አስገንዝበዋል።

መረጃው በአግባቡ ካልቀረበ ወጪ የተደረገው የመንግስት ገንዘብ ተመላሽ እንዲደረግ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም