ኢትዮጵያ ለጠፈር ምርምር ከዓለም መሪ መሆን የሚያስችል መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ አላት

1176

አዲስ አበባ ጥር 27/2011 ኢትዮጵያ በስነ-ፈለክ እና ጠፈር ምርምር ከዓለም መሪ መሆን የሚያስችል መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ እንዳላት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የጠፈር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከሌሎች አገሮች አንፃር ዘግይቶ ነው የተጀመረው።

በዚህም በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በተለይም በጠፈር ሳይንስና ስነ-ፈለክ ዓለም ከደረሰበት ደረጃ መድረስ የሚያስችል መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ እያላት በአግባቡ ጥቅም ላይ አልዋለም ብለዋል።

በመሆኑም በጠፈር ምርምርና ስነ-ፈለክ ከዓለም ቀዳሚ አገር ለመሆን ያላትን የተፈጥሮ ጸጋ በሰው ኃይልና በመሰረተ-ልማት ግንባታ ለመሙላት እንቅስቃሴ መጀመሯን ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በማስተባበር ለአብነት በመቀሌ፣ ባህርዳር፣ አዲስ አበባና አዳማ ዩኒቨርሲቲዎች የቴክኖሎጂ ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

“በዓለም ላይ አንዲት አገር በትክክል ወደ ጠፈር ምርምር የመግባቷ ማረጋገጫ የጠፈር ፖሊሲ ነው” ያሉት ዶክተር ሰለሞን ኢትዮጵያም በዘርፉ ፖሊሲ ካላቸው ስድስት የአፍሪካ አገሮች አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሹመቴ ግዛው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ለጠፈር ሳይንስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

መቀሌና አዳማ ዩኒቨርሲቲዎችን ለአብነት በመጥቀስ ከአምስት በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰው ኃይል የማፍራትና የመሰረተ-ልማት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት፣ ጥናትና ምርምር ለማድረግና ስልጠናዎችን ለመስጠት መቋቋሙንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የዘርፉን ምርምር ዘግይታ የጀመረች ቢሆንም በአፍሪካ ብሎም በዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን የራሷን የተፈጥሮ ጸጋ ማበልጸግ ይኖርባታል ነው ያሉት።

በመሆኑም በዓለም የጠፈር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ አገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ ዘርፉ ወደፊት እንዲራመድ እናደርገዋለን ብለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ በኢትዮጵያ በዘርፉ የሚከናወኑ ጉባኤዎችና ስብሰባዎች አቅምን ለማጎልበት ተጨማሪ ግብዓት ይሆናሉ።

ኮሪያና ቻይና የጠፈር ሳይንስን ሲጀመሩ ኢኮኖሚያዊ ዕድገታቸው ኢትዮጵያ አሁን ካለችብት አቅም በታች እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ሹመቴ፤ ጠፈር የዕድገታችን መሰረተ ነው ብለው በመነሳታቸው ዛሬ ከሃያላኑ ጎራ መቀላቀላቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም የጠፈረ ምርምርን እንደቅንጦት ከማየት የዕድገት መሰረት መሆኑን ተገንዝቦ ለዘርፉ መዳበር ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።