ሚኒስቴሩ በተደጋጋሚ ከተሰጡት የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች መሻሻል እያሳየ አይደለም

219

አዲስ አበባ ጥር 27/2011 የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ከተሰጡ የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ልምድና ተሞክሮ መሻሻል እያሳየ አለመሆኑን የፌዴራል ዋና ኦዲተር አመለከተ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሚኒስቴሩ በተደጋጋሚ የሚነሳበትን የኦዲት ግኝት በአፋጣኝ እንዲያስተካካል ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንዳሉት፤ በቅርቡ በአገሪቱ በተገነቡ 23 ዩኒቨርሲቲዎች እስከ ዛሬ የተሰጡ የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች አሁን በሚገነቡ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ አልተወሰደባቸውም።

በተደጋጋሚ የሚነሱ የዕቅድ አዘገጃጃት ችግሮች፣ ስራዎችን ከበጀት ጋር አጣጥሞ ያለመሄድና በበጀት ላይ የሚገጥሙ ችግሮችን አስቀድሞ ታሳቢ ያለማድረግ ፣ ለአንድ ተቋራጭ አፈጻጸሙ ሳይገመገም ተደጋጋሚ ስራ መስጠት የግንባታ ግብአት ማስቀመጫ ያለመኖር ለካሳ ክፍያ ዝርዝር መመሪያ ያለማስቀመጥ ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው።

በተጨማሪም የቅንጅት አሰራር ማነስ ፣ የተሟላ ማስረጃ ለሌላቸው ሰዎች ካሳ መክፈል ዋና ኦዲተሩ በችግር የለየው የክዋኔ ኦዲት ግኝት ነው።

እነዚህ ችግሮች ከዚህ ቀደም በተገነቡ ዩኒቨርሲቲዎች የኦዲት ግኝቱ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸው ችግሮች ቢሆኑም ለውጥ አልታየባቸውም።

እነዚህ ችግሮች አሁን በሚገነቡ ዩኒቨርሲቲዎች የታዩና ለቀጣይ ለሚገነቡ ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ስጋት የሚታዩ መሆናቸውን ዋና ኦዲተሩ ተናግረዋል።

በተነሱ ችግሮች ሳቢያ ሚኒስቴሩ ለዲዛይን ዝግጅት ከተያዘው በጀት ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይና ለዲዛይን ቁጥጥር አማካሪዎች ከተያዘው በጀት 28 ሚሊዮን ብር ውስጥ ከሶስት እጥፍ በላይ ክፍያ መፈጸሙን እንደማሳያ ወስደዋል።

በተጨማሪ በወራቤ ዩኒቨርሲቲ ከግንባታው ቦታ ላልተነሱ 17 አባወራዎች  የካሳ ክፍያ መፈጸምና  ቁጥራቸው በውል ለማይታወቁ አባወራዎች ክፍያ ከተፈጸመላቸው በኋላ በግንባታ ሳይት በድጋሚ መግባታቸው ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት ያለመስራት ማሳያ እንደሆነ ዋና ኦዲተሩ አስረድተዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ተናቦ ባለመስራቱ ከካሳ ጋር ተያይዞ ሰፊ ችግር መከሰቱን የኦዲት ግኝቱ አመላክቷል።

ዋና ኦዲተሩ እንዳሉት፤ አሁን ለምክር ቤቱ የቀረቡ የኦዲት ግኝቶች ጥቂቶቹ ሲሆኑ በቀጣይ ከግዥና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር የተደረጉ  የኦዲት ግኝቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲቀርብ ይደረጋል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ መሐመድ የሱፍ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ከአካባቢ ግንባታ ጋር የሚጣጣም ዲዛይን አለማዘጋጀት፣ ለተሰሩ ስራዎች የተሟላ መረጃ ያለማቅረብና ግንባታዎች ላይ ያለበትን ክፍተት በአፋጣኝ አለማስተካካል እንደችግር መታየቱን ገልጸዋል።

''ሚኒስቴሩ ያወጣውን መመሪያ ያለማክበር ደግሞ ሌላው የተቋሙ የአሰራር ግድፈት ነው'' ብለው በአፋጣኝ መስተካከል እንደሚገባው አሳስበዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ለተቋሙ የሚፈቀደው በጀት አነስተኛ በመሆኑ የተያዙትን የካሳም ሆነ ሌሎች ከፍያዎች በአግባቡ ማከናወን አለመቻሉን ገልጸዋል።

500 ሚሊዮን ብር ለመብራት ሃይል ከፍሎ አገልግሎቱን ባለማግኘቱ ዩኒቨርሲቲዎቹ ለተማሪዎቹ በበቂ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸውን ጠቁመዋል።

የተቋሙ የግብአት አቅርቦትን በተመለከተ አብዛኛውን ከውጭና ከአገር ውስጥ በማስገባት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ሲቻል የላብራቶሪ ግዥ  በተያዘው የጊዜ ገደብ ባለመፈጸሙ ተማሪዎች ወደ አጎራባች ዩኒቨርሲቲዎች ሄደው አገልግሎቱን ለማግኘት ተገደዋል።

በኦዲት ግኝቱ ሰነድ ሳይገኝባቸው ክፍያ የተፈጸመባቸውን አገልግሎቶች በ10 ቀን አጣርተው ለምክር ቤቱና ለዋና ኦዲተሩ ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም