የደሴ ከተማን ስፖርት ቡድን ለማጠናከር ያለመ ሀገር አቀፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር ተከፈተ

70

ደሴ ጥር 26/2011 የደሴ ከተማን ስፖርት ቡድን ለማጠናከር ያለመ ሀገር አቀፍ የንግድ ትርኢት፣ ኤግዚቪሽንና ባዛር በደሴ ከተማ ተከፈተ።

የደሴ ከተማን የእግር ኳስ ስፖርት ቡድን በገንዘብ ለመደገፍ ታልሞ የተዘጋጀው ባዛር የተከፈተው በደሴ ከተማ መርሆ ግቢ ነው።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰይድ አራጋው እንዳሉት በተዘጋጀው ባዛር ከስፖንሰር፣ ከትኬት ሽያጭና ከቦታ ኪራይ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡

"ክለቡ ከብሔራዊ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ቢሸጋገርም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ጥሩ ተጫዋትና አሰልጣኝ መግዛትና መቅጠር ባለመቻሉ ውጤቱ አሽቆልቁሎ ከ12ቱ ቡደኖች 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል" ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የቡድኑን አሰልጣኝ መሰናበቱን ጠቁመው በሚሰበሰበው ገቢ ጥሩ  አሰልጣኝና ተጫዋቾችን ለመግዝታ መታሰቡን ገልጸዋል፡፡

የተከፈተው በዛር ለ15 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከ100 በላይ ነጋዴዎችን እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።

"ባዛሩ የከተማውን የንግድ እንቅስቃሴ በማነቃቃት አምራችና ሸማቹን ማህበረሰብ በቀጥታ በማገናኘት ህብረተሰቡንም ተጠቃሚ ያደርጋል" ብለዋል፡፡

በባዛሩ ታዋቂ ድምጻዊያን ዳኘ ዋለ፣ ሚኪያስ ቸርነት፣ ጸጋዬ እሸቱን ጨምሮ የተለያዩ ድምጻዊያን የሚታደሙ ሲሆን "በአማራ ክልል ፖሊስ ባንድና በወሎ ኪነት ቦድኖችም ደምቆ ይሰነብታል" ብለዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ተስፋዬ ጫኔ በበኩላቸው "ባዛሩ ከ40 በላይ ለሚሆኑ የከተማው ስራጥ ወጣቶች ጊዜያዊ የሥራ እድል ከመፍጠሩ ባለፈ የከተማውን የንግድ እንቅስቃሴ ያነቃቃል" ብለዋል፡፡

የስፖርት ቡድኑን ለማጠናከር ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ቢያዝም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ከሌሎች ቡድኖች ጋር እኩል ተወዳዳሪ ባለመሆኑ በተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢዎች ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡

በተዘጋጀውንግድ ትርኢትና ባዛር ከሚሳተፉ ነጋዴዎች መካከል ወይዘሮ ሰዓዳ አብደላህ ከአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ምርቶችን ይዘዉ መቅረባቸዉን ተናግረዋል፡፡

የወለል ምንጣፍ፣ ጭሳጭስና የተለያዩ ረከቦቶችን ለተጠቃሚ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ በ15 ቀን ቆይታቸው የተሻለ ትርፍ ለማግኘት ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በደሴ ከተማ የቀበሌ 05 ነዋሪ አቶ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው ባዛሩ በደሴ ከተማ በቀላሉ የማይገኙ እቃዎችን ለማግዛት ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የደሴን እግር ኳስ ቡድን ለማጠናከር በ2009 ዓ.ም በተዘጋጀው የንግድ ትርኢትናና ባዛር 4 ሚሊዮን የሚጠጋ የተጣራ ገቢ ተገኝቶ እንደነበረ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም