የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማይናጋ መሰረት ላይ ለመጣል ግብር ከፋዩ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል.....ወይዘሮ አዳነች አበቤ

122

ባህር ዳር ጥር 26/2011 የኢትዮጵያን ኢኮኖሚዋ በማይናጋ መሰረት ላይ ለመገንባት ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የውዴታ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የገቢዎች ሚኒስቴር ወይዘሮ አዳነች አበቤ ገለጹ።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የ2011 በጀት ዓመት የግብር ህግ ተገዥነትን ለማሳደግ የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ አስጀምሯል።

"ግዴታዬን እወጣለሁ፣ መብቴን እጠይቃለሁ" በሚል መሪ ቃል በተጀመረው የንቅናቄ መድረክ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አበቤ እንደገለጹት በኩሩ ህዝቦቿ ተጋድሎ ማንነቷ ተከብሮ የኖረችው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ድሃ ከሚባሉት አገራት ተርታ ትገኛለች።

"ይህን ስሟን ለማስቀየርና ኢኮኖሚዋ በማይናጋ መስረት ላይ እንዲገነባ ለማድረግ ግብር ከፋዩ ሕብረተሰብ በፍላጎትና በአገራዊ ፍቅር ስሜት ከሚያገኘው ገቢ ላይ ለመንግስት ግብርን መክፈል አለበት" ብለዋል።

በአገሪቱ የተከሰተውን ለውጥ ምክንያት በማድረግ ለውጡ ጥቅማቸውን የነካባቸው አካላት ሰላም እንዲደፈርስና የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር ግብረ በአግባቡ እንዳይከፈል እያደረጉ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግዋል።

" ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ግብር መክፈል ለራሱና ለሚወዳት አገሩ መሆኑን ተገንዝቦ ኃላፊነቱን ከመወጣት ባለፈ እንደ ጥንት አባቶች አንድነቱን አጠናክሮ መንቀሳቀስ ይኖርበታል " ብለዋል።

የአማራ ክልልም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የፌዴራል መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብዙአየሁ ቢያዝን በበኩላቸው በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ግብር በአግባቡ እየተከፈለ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

እንደርሳቸው ገለጻ ክልሉ ባለፈው ግማሽ በጀት ዓመት ስድስት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ መሰብሰብ የቻለው 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ነው።

በርካታ ነጋዴ ያለደረሰኝ እንደሚሸጥና የህብረተሰቡ ለሚገዛው እቃ ደረሰኝ የመጠየቅ ልምድ አናሳ መሆን፣ ህገ-ወጥ ደረሰኝ በመጠቀም ከመንግስት ካዝና ያልተገባ ተመላሽ መጠየቅና፣ የክልሉን ሰላም ሆን ተብሎ እንዳይረጋጋ ማድረግ ግብር ላለመክፈል ሲደረጉ የነበሩ አሻጥሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

"ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የክልሉ ህዝብ  ባለፉት ዘመናት ሲደርስበት በነበረ በደል እንዲቆዝምና ግብር መክፈል እንደሌለበት የሚሰሩ አካላትም  አሉ" ብለዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው  "የህብረተሰቡ ግብር የመክፈል ዝንባሌ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢሆንም ከኢኮኖሚው እድገት አኳያ አሁንም የሚሰበሰበው ግብር ውስንነት አለበት" ብለዋል።

የመንግስት ሠራተኛው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ግብር እየከፈለ መሆኑን ጠቁመው ነጋዴው ህብረተሰብም ግብር መክፈል የመብትና የግዴታ ጉዳይ ሳይሆን ኩራትም ጭምር መሆኑን አውቆ አገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በሚሰሩ ስራዎች መላው ህብረተሰብ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ በክልሉ የተጀመረው የንቅናቄ መድረክ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 የሚቀጥል ሲሆን ሁሉንም የክልሉን ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚያ ዳርስም ተገልጿል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የጸጥታ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና  የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

ሀገር አቀፍ የታክስ ንቅናቄ መድረክ ባለፈው ታህሳስ ወር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሀመድ "ግዴታየን እወጣለሁ፣ መብቴን እጠይቃለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም