ወላይታ ድቻ የመጀመሪያው የቮሊቦል ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ ሆነ

56

አዲስ አበባ ጥር 26/2011 ወላይታ ድቻ የመጀመሪያው የቮሊቦል ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ ሆኗል።

በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽንና በጎንደር ከተማ አስተዳደር አዘጋጅነት ከጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በጎንደር ከተማ ሲካሄድ የቆየው ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።

በውድድሩ በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ አምስት ክለቦች ተካፍለዋል።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ብሩህ ተክለኃይማኖት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በውድድሩ መዝጊያ የፍጻሜና የደረጃ ጨዋታዎች ተካሂደዋል።

በፍጻሜው የተገናኙት ወላይታ ድቻና መከላከያ ባደረጉት ጨዋታ የአምናው የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ወላይታ ድቻ በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 0 አሸንፏል።

መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲና አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባደረጉት የደረጃ ጨዋታ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል።

የክለቦችን የውድድር መድረክ በማስፋት ምርጥ ስፖርተኞች ለማፍራትና ስፖርቱ በቀደምት ዓመታት የስፖርቱ እድገት ይታይበት የነበረውና በአሁኑ ሰዓት የስፖርቱ እንቅስቃሴ የተዳከመበትን የጎንደር ከተማ ወደ ቀድሞው ዝና መመለስ የውድድሩ ዓላማ እንደሆነም ተገልጿል።

የውድድሩ አሸናፊ ወላይታ ድቻ የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ሲሸለም መከላከያና መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ በቅደም ተከትል የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።

በውድድሩ ፍጻሜ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽንና የጎንደር ከተማ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች ለተሳታፊዎች የተዘጋጀውን ሽልማት አበርክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም