በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች አዲስ የአቅርቦት ስርዓት እንዲዘጋጅላቸው የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ

70

ደብረ ብርሃን ጥር 26/2011 መንግስት ለህብረተሰቡ በድጎማ የሚያቀርበው መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃ ከህዝቡ ቁጥር ጋር ያልተጣጣመ በመሆኑ አዲስ የአቅርቦት ስርዓት ይዘጋጅልን ሲሉ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በከተማው የፍጆታ ሸቀጦችን ከሚያከፋፍሉ ቸርቻሪዎች፣  ከሸማች ማህበራትና ከህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር ትናንት ተወያይተዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ስኳርና ዘይት ተወክለው እንደሚያከፋፍሉ የገለጹት መቶ አለቃ ከፈለኝ ወልደፃዲቅ ለ8 ቤተሰብ 6 ኪሎ ስኳር እንዲሁም 3 ሊትር ዘይት መሰጠቱ ከቤተሰብ ቁጥርና ፍላጎት ጋር እንደማይጣጣም ተናግረዋል።

አቅርቦቱ የነዋሪውን ቁጥር ግምት ውስጥ ያስገባ ካለመሆኑ ባለፈ በተለይ ስኳር ወቅቱን ጠብቆ ስለማይቀርብ ከተጠቃሚ ህብረተሰብ ጋር መተማመን እንዳይኖር ማድረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይ ችግሩ እንዲፈታ ለከተማው አዲስ የአቅርቦት ስርአት  መዘርጋት እንደሚገባ አመልክተዋል። 

በከተማው የቀበሌ 08 ነዋሪ አቶ ገበየሁ ሳህለ በበኩላቸው መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ለዳቦ ጋጋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ዱቄቱን ቢያቀርብላቸውም የሚሸጡት የዳቦ መጠን ከ100 ግራም በታች መሆኑን ገልጸዋል።

በስርጭት በኩልም የህዝቡን ፍላጎት የሚያረካ እንዳልሆነ ጠቁመው ላልተገባ ጥቅም በሚስገበገቡ ግለሰቦች ላይ መንግስት ተገቢውን አርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

ለከተማዋ የተመደበው የፍጆታ ዕቃ መጠን ታይቶ የሚሻሻልበትን መንገድ መፍጠር እንደሚገባም አመልክተዋል 

የደብረ ብርሃን ከተማ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ቹቹ ዘመላክ በበኩላቸው በህብረተሰቡ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ተገቢ መሆናቸውን ገልጸው "በአጥፊዎች ላይ አርምጃ እየተወሰደ ነው" ብለዋል።

ለከተማው ህብረተሰብ  ዳቦ ጋግረው ለማቅረብ ከመንግስት በተመጣጣኝ ዋጋ ዱቄት የሚረከቡ 21 ዳቦ ቤቶች ቢኖሩም በተደረገ የሚዛን ጥራትና አቅርቦ ፍተሻ 15ቱ ህብረተሰቡን በተገቢው መንገድ እያገለገሉ እንዳልሆነና በእዚህም ከባድ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አብራርተዋል።

የዞኑ ንግድ መምሪያ የሸማቾች ጥበቃና ድጋፍ ቡድን መሪ አቶ ጠገናው ደበበ በበኩላቸው በህብረተሰቡ ከአቅርቦት ጋር የተነሱ የፍታሃዊነት ችግሮች አግባብ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ለሚኖር ከ2 ሚሊዮን 994 ሺህ በላይ ህዝብ በ45 ቀን 11ሺህ 327 ኩንታል ስኳር ብቻ መቅረቡ ችግሩ እንዲከሰት ማድረጉን አመልክተዋል

የፓልም ዘይትም ቢሆን በተመሳሳይ በወር 562ሺህ 300 ሊተር እንደሚቀርብ ገልጸው አሁን ካለው የዞኑ ህዝብ ቁጥር ጋር የማይጣጣምና የቤት ተከራዮችን ተጠቃሚ ያላደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ከ10 ዓመት በፊት የነበረው የፍጆታ እቃዎች የኮታ መጠን የድልድል ማነስ ፍትሃዊነት የጎደለው ስርጭት እንዲኖር ያማድረጉንም ጠቁመዋል።

" በስንዴ ዱቄት በኩልም ለህብረተሰቡ በወር የሚቀርበው 3ሺህ 139 ኩንታል ብቻ በመሆኑ የህብረተሰቡን ፍላጎት ማርካት አልተቻለም ፤ የኮታ ድልድሉ እንደገና የሚታይበት ሁኔታ ይኖራል" ብለዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባልና የቡድኑ አስተባባሪ አቶ ዋሲሁን ታደሰ በበኩላቸው "ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋል" ሲሉ ገልጸዋል። 

ሁሉም ጥያቄዎች በየደረጃው ምላሽ እስኪያገኙ ህብረተሰቡ ፍታሃዊ የንግድ ስርዓት እንዲኖርና የአካባቢው ሰላም እንዲጠናከር የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም