የጸጥታ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ከመንግስት ጋር ተባብረን እንሰራለን---በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች

79

ፍቼ  ጥር 26/2011 የፀጥታ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ከመንግስት ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን  ነዋሪዎች ገለጹ።

ከወረዳዎ የተለያዩ ቀበሌዎች የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የሰላም ኮንፈረንስ ተጠናቋል።

በዞኑ ደገምና ወረጃርሶ ወረዳ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የሀገር ሽማግሌዎች ለሁለት ቀናት በየአካባቢያቸው ያካሄዱትን የሰላም ኮንፈረንስ ትናንት ሲያጠናቅቁ ባወጡት የአቋም መግለጫ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን ተገን በማድረግ ሰላምን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የፀጥታ አስከባሪ አካላት በህዝቡ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከመጠበቅ ባለፈ ከህብረተሰቡ የሚያገኙትን ጥቆማ መሰረት አድርገው ጥፋት የሚያደርሱ ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል የህግ የበላይነትን ማስፈን እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የችግር ፈጣሪዎች ፍላጐት የህዝብን ሰላም ማወክና በአሁኑ ሰዓት እየታየ ያለውን የለውጥ ጉዞ ማደናቀፍ በመሆኑ ድርጊቱን እንደሚታገሉም በመግለጫቸው ላይ አረጋግጠዋል።

በቅርቡ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና በኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) መካከል የተደረገው ስምምነት የኦሮሞን ህዝብ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ጥቅሙን ለማስከበር የሚረዳ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ አብረው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

በኦሮሞ አባ ገዳዎች  ሸምጋይነት  የተደረገው እርቅና ስምምነት የኦሮሞ ህዝብ የራሱን ችግር በራሱ የመፍታት የቆየ ባህሉን የሚያንፀባርቅ በመሆኑም እንደሚደግፉት ተናግረዋል።

ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል የወረጃርሶ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሚኒሻ ቱፋ  የተጀመረውን የመደመርና የለውጥ ጉዞ በማፋጠን የህግ የበላይነትን ለማስፈን በስነ ምግባር የታነፀ ዜጋ በማፍራት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ በኮንፈረንሱ ላይ ቃል ገብተዋል።

የደገም ወረዳ የሀምቢሶ ከተማ ነዋሪ ሻምበል ሽፈራው በበኩላቸው ተፈቃቅሮና ተከባብሮ የሚኖረውን ህዝብ ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለማጋለጥ ከፀጥታ ኃይሎች ጐን ተሰልፈው እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡

" አልፎ አልፎ በአካባቢያቸው የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች እንዲፈቱና ጥፋት የሚያደርሱ አካላት እንዲጠየቁ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጐን ተሰልፌ እሰራለሁ " ያሉት ደግሞ የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ሚልኪቱ ቶለሣ ናቸው፡፡

በተለይ ወጣቶች ውይይትና ምክክርን በማስቀደም ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ በመምከር አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አበራ ወርቁ በበኩላቸው የዞኑ ነዋሪ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አድንቀው ይህም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚሰራውን ተግባር እንደሚያግዝ ጠይቀዋል።

ለሁለት ቀን በተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ላይ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከወረዳዎቹ የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም