በግራር ጃርሶ ወረዳ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን የተጠቀሙ አርሳ አደሮች ምርታማ መሆናቸውን ተናገሩ

127

ፍቼ ጥር 26/2011 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ በመስመር የዘሩና የተሻሻሉ የምርት ማሳደጊያዎችን የተጠቀሙ አርሶ አደሮች የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ተናገሩ።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት በበኩሉ በዞኑ በመኸር ሰብል ከተሸፈነ መሬት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ  ምርት መገኘቱን አስታውቋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች እንዳሉት በ2010/2011 የመኸር እርሻቸው የተሻለ ምርት ማግኘት የቻሉት ለምርት እድገት አስተዋፅኦ ያላቸውን የግብርና ዘዴዎች በመጠቀማቸው ነው።

በመስመር የመዝራት ዘዴን ተግባራዊ ካደረጉአርሶ አደሮቹ መካከል በወረዳው የወርጡ ቀበሌ አርሶ አደር ወሰና በቀለ እንዳሉት ከአንድ ሄክታር በብተና ከሚዘሩት ማሳ ቀደም ሲል ከ17 ኩንታል የማይበልጥ  ምርት ያገኙ ነበር።

በመኸሩ ማሳቸውን ሙሉ ለሙሉ በመስመር በመዝራታቸው ዘንድሮ ከእጥፍ በላይ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በ2009/2010 የመኸር እርሻ አራት ሄክታር መሬታቸውን ለሁለት ከፍለው ግማሹን በብተና ቀሪውን በመስመር እንደዘሩ የተናገሩት ደግሞ የጊኖ ቀበሌ አርሶ አደር ደጀኔ ፉላሳ ናቸው።

“በብተና ከዘራሁት ከሄክታር 15 ኩንታል ጤፍ ሳገኝ በመስመር ከተዘራው በሄክታር ከ40 ኩንታል በላይ ጤፍ አግኝቺያለሁ” ብለዋል።

እንደ አርሶአደር ደጀኔ ገለጻ ባለፈው ክረምት ያላቸውን ማሳ ሙሉ ለሙሉ በመስመር በመዝራታቸውና የዝናቡ ሁኔታ የተስተካከለ በመሆኑ ምርታቸውን ወደ አንድ መቶ ኩንታል ከፍ ማድረግ ችለዋል ።

የተሻሻለ የግብርና አሰራር ምርታማ ከማድረጉ በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በከንቱ መሬት ላይ ባክኖ እንዳይቀር የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

የጤፍ ችግኝን በመደብ አዘጋጅተው ለመጀመሪያ ጊዜ በመኸር እርሻ እንደተከሉ የተናገሩት የእዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ደርቤ አሰፋ በበኩላቸው “በእዚህ ዘዴ በሄክታር የማገኘውን የጤፍ ምርት ከ15 ወደ 38 ኩንታል ማሳደግ ችያለሁ” ብለዋል።

ሌሎች አርሶ አደሮችም ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቅመው በመደብ ችግኝ አፍልተው  በመስመር ቢተክሉ ጥሩ ምርት እንደሚያገኙ መክረዋል ።

በመስመር የመትከል ዘዴ ተጠቅመው ለሦስተኛ ጊዜ የዘሩት ጤፍ ጥሩ ምርት እንዲሰበሰቡ ያደረጋቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ በወረዳው የቶርባን አሼ አርሶ አደር ደምሴ ደንደና  ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም በክረምቱ የመኸር እርሻ ያለሙትን ሰብል ሙሉ ለሙሉ በመሰብሰብ ለበልግ እርሻ ዝግጅት አያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል 

የግብርና በለሙያዎች የሚሰጧቸው ምክርና እገዛ ለእርሻ ሥራቸው ምርት እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉንም ገልጸዋል ።

በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማትና ኤክስቴንሽን ቡድን መሪ አቶ ደረጄ ኤጀታ በዞኑ 13 ወረዳዎች ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደእርሳቸው ገለጻ በሰርቶ ማሳያዎች በተከናወኑ ሥራዎች ሰብልን በመስመር በመዝራት፣ በመትከልና ቅልቅል ማዳበሪያን በመጠቀም የግብርና ሥራውን ማከናወን ለምርት እድገት አስተዋፅኦ እንዳለው በአርሶ አደሩ ዘንድ ግንዛቤ ተይዟል ።

በእዚህም በዞኑ በ2010/2011 የምርት ዘመን ምርታማነትን ለመጨመር በሰብል ከተሸፈነው 429 ሺህ 773 ሄክታር መሬት ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው በመስመር የመዝራት ዘዴን ተከትሎ በሰብል የተሸፈነ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህም በሰብል ከተሸፈነው መሬት ከ12 ሚሊዮን 667ሺህ  ኩንታል በላይ  የእህል ምርት እንዲገኝ  መርዳቱን ነው ቡድን መሪው የገለጹት።

እንደአቶ ደረጄ ገለጻ በእርሻ ሥራው 176 ሺህ 680 አርሶ አደሮች የተሳተፉ ሲሆን በጥቂት ቀበሌዎች ከታየው የዝናብ  እጥረት በስተቀር በአበዛኛው የዞኑ አካባቢዎች በክረምት ወቅት ለእርሻ ሥራ ተስማሚ የሆነ ዝናብ መጣሉ ለምርቱ እድገት አስተዋጽኦ አድርጓል።

በ2009/2010 የመኸር እርሻ በሰብል ከተሸፈነው መሬት ከ9 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት የተገኘ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት አርሶ አደሮች የተሻለ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን መጠቀማቸው ምርቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም