በአዲስ አበባ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እየተስፋፉ ነው - ጥናት

132

አዲስ አበባ 25/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ መጤና አደገኛ ልማዳዊ ድርጊቶች በአሳሳቢ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ መሆናቸውን አንድ ጥናት አመለከተ። 

10ኛው የከተማ አቀፍ የባህል ሳምንትን ምክንያት በማድረግ የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ  ባዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ የቀረበው ይኸው ጥናት እንደጠቆመው አደገኛ የሆኑት ልማዳዊ ድርጊቶቹ እንዲስፋፉ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል ዋናው የህግ  መላላት ነው። 

በቢሮ የባህል ጥናት እሴት ባለሙያ አቶ ሸዋደግ ብርሃኑ ጥናቱን ባቀረቡ ወቅት፣ የተመሳሰይ  ጾታ የወሲብ ግንኙነት፣  የራቁት ዳንስ ቤቶች፣ ሺሻን ጨምሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ የጫትና የመጠጥ ቤት በስፋት መኖር አደገኛ ከሆኑት ተግባራት መካከል ናቸው ብለዋል። 

ችግሩን ለመከላከል ያለው የህግ ማእቀፉ የላላ መሆኑ ተግባሩን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት መፍጠሩም ተመልክቷል።

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ብቻ በአንድ ቀን የተመሳሳይ  ጾታ የወሲብ ግንኙነት የሚደረግበትና የሺሻና የጫት ንግድ የሚጧጧፍባቸው 54 ቤቶች እንዲዘጉ ቢደረግም በሶስተኛው ቀን  ባልታወቀ ምክንያት ተመልሰው መከፈታቸውን ለአብነት አንሰተዋል። 

በቱሪስት መልክ ወደ አገር የሚገቡ የውጭ ዜጎችም በተለይ የግብረሰዶም ተግባር እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ነው በጥናቱ የተመለከተው። 

በአዲስ አበባ ከመጀመሪያ እስከ ሁለተተኛ ደረጃ ያሉ በተለይ የግል ትምህርት ቤቶች ለተለያዩ ተባራት ቀን በመሰየም የሚያዘጋጇቸው ሁነቶችና የሚከታተሏቸው ፊልሞች ለችግሩ መባባስ አስተዋፅኦ እንዳላቸውም ተገልጿል።

የመንግስት በአደንዛዥ እጽ ዝውውር ላይ ጥብቅ ቁጥጥር አለማድረግ፣ የሺሻ እቃዎች ወደ አገር እንዲገቡ መፍቀድ ለችግሩ መንስኤ መሆናቸውም ተጠቁሟል።

ችግሩን በንቅናቄ ጭምር ለመቀነስ ከዚህ በፊት የተደረጉት ጥረቶች ውጤት አለማምጣታቸውን የጠቆመው ጥናቱ ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት ወላጆች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሚዲያዎችና መንግስት ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

የመንግስትና የግል የሚዲያ ተቋማትም የችግሩን ጥልቀት በማየት በሰፊው አጀንዳ ቀርጸው ሊረባረቡ እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ ሃሳባቸውን አንስተዋል።

በሲምፖዚየሙ ላይ የሃይማኖት ተቋማት፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው ተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ ከሁሉም ክልል የተጋበዙ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም