በኢትዮጵያ የስራ ላይ ደህንነት አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል ተባለ

342

አዲስ አበባ ጥር25/2011 በኢትዮጵያ የስራ ላይ ደህንነት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ ተገለጸ።

በአገሪቱ በተለይም የግንባታ፣ የማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ የጤና ተቋማት፣ የቁፋሮና የፋብሪካ ስራዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚያስፈልጋቸው ዘርፎች ይመደባሉ።

እነዚህ የስራ ዘርፎች የአገሪቱን ዕድገት ተከትሎ እየተስፋፉና ለብዙ ዜጎችም የስራ ዕድል እየፈጠሩ መሆኑ የማይካድ ነው።

ለአብነትም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በግንባታ ዘርፍ መሰማራታቸውን ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ከትራንስፖርት ዘርፍ ቀጥሎ ከሚደርሱ የስራ ላይ አደጋዎች በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውም የግንባታው ዘርፉ ነው። እንዲህም ሆኖ ዘርፉ ከፍተኛ የሥራ ላይ ደህንነት አደጋ የተጋረጠበት ሆኗል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የህግና ፌዴራሊዝም ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ተስፋዬ አባተ ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት አባል አገሮች የአገራቸውን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት በማድረግ የስራ ላይ ደህንነትና ጤንነት ህጎችን እንዲያወጡ ይገደዳሉ ይላሉ።

የወጡ ህጎች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት መጣሉን ነው የገለጹት።

“ኢትዮጵያም የድርጅቱ አባል እንደመሆኗ የስራ ላይ ደህነነትና ጤንነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባት፣ ለዚህም ነው በህገ-መንግስቷ ላይ በግልጽ ያስቀመጠችው፤ ህጎችንም ያወጣችው” ብለዋል።

''ህገ-መንግስቱ ላይ በተለይ አንቀጽ 42 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ በዋናነት ሰራተኛው ጤናማና ከአደጋ ነጻ የሆነ የስራ አካባቢ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ ተደንግጎ እናገኛለን። እንግዲ የአገር ውስጥ ህጎቻችን ከዚህ ነው የሚጀምሩት ማለት ነው።''

እንደ ዶክተር ተስፋዬ ገለጻ በኢትዮጵያ የስራ ላይ ደህንነትና ጤንነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የአሰሪና ሰራተኛ ህጎችና አዋጆች ወጥተዋል።

''በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ውስጥ ይሄም ተቀምጦ እናገኛለን በተለይ በአንቀጽ 92 ንዑስ አንቀጽ አንድ ስር ቀደም ሲል በተደነገገው መሰረት የአሰሪውንና የሰራተኛውን ግዴታዎች ያስቀምጣል። አሰሪው በዋናነት ስለሙያ ደህንነትና ጤናማነት የተደነገጉ ሁኔታዎችን የማክበር ሃላፊነት ይኖርበታል።ይሄንን ወደ ተግባር ለመቀየር ደግሞ መሟላት ያለባቸውን ነገሮች የማሟላት ሃላፊነት ያለበት ስለመሆኑ ተቀምጧል።ህክምና የመስጠት ለደረሰው ጉዳት ደግሞ አግባብነት ያለው ካሳ መከፈሉን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው የሚሆነው  ከደረሰው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ መከፈል ያለበት ስለመሆኑ በተለይ የፍትሃብሄር ህጉ የሚያስቀምጠው።''

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ህጎቹ ወደ ተግባር መቀየራቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር ህጋዊ ኃላፊነት እንዳለበትም ነው ያመለከቱት።

በኢትዮጵያ የስራ ላይ ደህንነትን በተመለከተ የወጡ ህጎች ተግባራዊ ባለመሆናቸው ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን የሚገልጹት ደግሞ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ናቸው።

''የሰራተኛ የሙያ ደህንነትና ጤንነት በኢትዮጵያ ውስጥ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል።ሁሉም ሰው እያየው ባለው መሰረት  በየቀኑ የሚደርሱ የስራ ላይ አደጋዎች እየጨመሩ ነው ያሉት።በኬሚካልም በማሽንም እጁን የሚቆረጥ አለ።በኬሚካል የሚጎዳ አለ።ከዚያ በተረፈ ደግሞ በኮንስትራክሽን ስራዎች ላይ ከፎቅ ላይ በመውደቅ  ከፍተኛ አደጋዎች እየደረሱ ነው ያሉት።''

ከሁለት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ፖሊሲ የወጣ ቢሆንም እስካሁን ተፈጻሚ አለመሆኑን ያነሳሉ።

''ፖሊሲው የሚያመላክተው በሁሉም የስራ ቦታዎች አስፈጻሚ አካላት ቁጥጥር ያደርጋሉ በሁሉም የስራ ቦታዎች ማለት ግንባታዎችንም ሌሎች ፋብሪካዎችንም የአበባ ድርጅቶችም ሊሆኑ ይችላል በሁሉም ቦታዎች ለመድረስ ነው ፖሊሲው የወጣው ይሄ ግን እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም ወደ አፈጻጸም አልተገባም።የተወሰኑ የህግ ክፍተቶች አሉ።ክፍተቶቹ ምንድነው የሚጣለው ቅጣት ትንሽ ነው የሙያ ደህንነትና ጤንነት አላከበርክም ተብሎ በፊት አንድ ሺ 200 ብር ነው የሚቀጣው አሰሪው።''

የፌዴራል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሰራተኞች የሙያ ደህንነትና ጤንነት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ነው ያስታወቀው።

በአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱም በየዓመቱ የ40 ሺህ ድርጅቶችን የሙያ ደህንነትና ጤንነት አጠባበቅ ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስቀምጧል።

በሚኒስቴሩ የሙያ ደህንነት ጤንነትና የስራ አካባቢ ጥበቃ ቡድን አስተባባሪ አቶ መስፍን ይልማ

''በስራ ላይ ሰራተኞችን ከአደጋ  ከጤና ጉዳት የመጠበቅ አገልግሎት እንደ አንድ የመንግስት አገልግሎት የሙያ ደህንነትና ጤንነት አጠባበቅ በሚል በመንግስት ይሰጣል ፤ ይሄ ቁጥጥር ምንድነው የስራ አካባቢው ለአደጋ የተመቻቸ ሁኔታ አለ ወይ የአደጋው ስጋት ደረጃ ይታይና በምን ሁኔታ ነው ሰራተኞችንና ንብረትን ከአደጋ መጠበቅ የሚቻለው ለሰራተኞቹ ተገቢው የአደጋ መከላከያ መሳሪያ ተሰጥቷል ወይ በቂ የሆነ ስልጠና አግኝተዋል ወይ ስራው ስለሚያስከትለው ጉዳት በደንብ ግንዛቤ ወስደዋል ወይ የሚለውንና የተለያዩ የስራ አካባቢውን የሚመለከቱ ሁኔታዎችን በዝርዝር የሚያዩበት ሁኔታ አለ።ይህን የሚከታተሉት የስራ ሁኔታ ተቆጣጣሪዎች ይባላሉ። ወደ 537 አሉ 2010 ላይ ባለን መረጃ መሰረት።''

አሰሪዎች የሰራተኞቻቸውን የስራ ላይ ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ቢጣልባቸውም ግዴታቸውን በማይወጡ ድርጅቶች ላይ እስካሁን የተወሰደው እርምጃ በጣት የሚቆጠር ነው ይላሉ አቶ መስፍን።

ለዚህ ደግሞ ሚኒስቴሩ ቅድሚያ የግንዛቤ ስራዎች አለመሰራታቸውንና የቅጣቱን ማነስ በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

''የሌላ አገር ህጎችን በምናይ ጊዜ ቅጣት ብቻ ሳይሆን እስርም አለ።የኛ ግን ደረጃውን ጠብቆ እንዲሄድ አስተማሪ የሆነ ቅጣት እንዲያገኙ መደረግ መቻል አለበት።አስተዳደራዊ የሆኑ እርምጃዎች በየጊዜው መወሰድ አለባቸው ከህጉ እርምጃ በፊት አስተዳደራዊ እርምጃዎች በተቆጣጣሪ ኮንትራክተሮች ሊወሰዱ ይገባል የህግ ማሻሻያዎች ማስጠንቀቂያዎች ሊወሰዱ ይገባል እነዚህን ነገሮች አጠናክረን እንሄዳለን።''

በስራ ላይ ለሚደርስ የህይወት ማለፍ የሚከፈለው የካሳ ክፍያ የአምስት ዓመት ደመወዝ ብቻ መሆኑንም ልብ ይሏል።

ባደጉት አገራት የኢንሹራንስ ተቋማት አባሎቻቸውን ከሚያስከፍሉት ዓመታዊ መዋጮ ውስጥ የስራ ላይ አደጋን መከላከል ተብሎ የሚቀመጥ ተቀማጭ አለ።

ይህ መዋጮ የስራ ላይ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚሰሩ ስራዎችን ለመደገፍና አደጋው ሲከሰትም አፋጣኝ ህክምና ለመስጠት የሚውል ነው።

በኢትዮጵያ ያሉ የኢንሹራንስ ተቋማት ይህን ተሞክሮ በመውሰድ ለስራ ላይ ደህንነት የድርሻቸውን እንዲወጡ አቶ መስፍን ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፉት አራት ወራት በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉት ግንባታዎች የስድስት ሰዎች ህይወት አልፏል። 11 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል።

በፍትሃ-ብሄር ህግ አንቀጽ 2548 ላይ አሰሪዎች ለሠራተኞቻቸው አካላዊ ደህንነት ተገቢ የሆነ የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም