የጎፋ ዞን ተመሰረተ

75

ሶዶ ጥር 24/2011 የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የጎፋ ዞን ተጠባባቂ ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ።

የጎፋ ዞን ዛሬ በይፋ ተመስርቷል።

የዞኑ ይፋዊ የምስረታ በዓል በሳውላ ከተማ ሁለገብ ስታዲየም የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የዞኑ ነዋሪዎች በተገኙበት ዛሬ ተከብሯል፡፡

የምስረታ በዓሉ በሃገር ሽማግሌዎች ምርቃት የተከፈተ ሲሆን ለረጅም ዘመናት በነዋሪው ዘንድ ሲነሳ የነበረ በዞን የመደራጀት ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ መመለሱ ሀገራዊ ለውጡን ህዝባዊ ያደርጋል ተብሏል፡፡

የዞኑ ተጠባባቂ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ አዳኝ ባደረጉት ንግግር "በትውልድ ቅብብሎሽ ሲነሳ የነበረው በዞን የመደራጀት ጥያቄ በመንግስትና በመሪው ድርጅት ደኢህዴን ምላሽ አግኝቶ በይፋ ምስረታው መበሰሩ የሚያስደስት ነው" ብለዋል፡፡

እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ የመዋቅር ጥያቄ መመለሱ በመንግስት ላይ ሆነ እርስ በርስ ከጥርጣሬ በመውጣት ሃገራዊ አንድነቱን በእውነተኛ መንፈስ ይበልጥ ለማጠናከር ያግዛል።

ህዝብ የተማረረበትን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በቂ አደረጃጀት በመፍጠር በቅርበት ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እርካታ ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ወጣቱ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በትዕግስት ከማለፍ ባለፈ በሃሳብ የበላይነትና ልዕልና ተመስርቶ የመደማመጥ ባህልን ሊያዳብር እንደሚገባም አመልክተዋል።

ነባሩን የመከባበር ባህል በመጠቀምና ልማቱን በማፋጠን ከመንግስት ጎን መቆም አንዳለበትም ነው ያሳሳቡት፡፡

በዓሉን በጸሎት የከፈቱት የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው ህዝቡ የሀገሩን ሰላም በመጠበቅ የታቀዱ የልማት ውጥኖች ተግባራዊ እንዲሆኑ አንድነቱን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎቹ እንዳሉት የአገሪቱን ዕድገትና ልማት በዘላቂ መሰረት ላይ ለማቆም ሰላምን መንከባከብ ያስፈልጋል።

ለእዚህም በአሁኑ ወቅት የተገኘውን የተሻለ ዕድል በመጠቀም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ እያንዳንዱ የዞኑ ነዋሪ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

ጎፋ ዞን ለመሆን ብዙ ዘመናት ቢያስቆጥርም በአሁኑ ወቅት ውሳኔ ማግኘቱ መንግስት የህዝብን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየፈታ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት የጀመረው የለውጥ ጉዞ  ህዝብን ተጠቃሚ እንዲያደርግ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም የሀገር ሽማግሌዎቹ ገልጸዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ተገኝተው የዞኑን ምስረታ ያበሰሩት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የደቡብ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ክፍሌ ገብረማሪያም ናቸው።

ቀደም ሲል ሁኔታዎች ባለመመቻቸት ምክንያት የህዝቡ ጥያቄ ሳይመለስ ቢቆይም በዘላቂነት ለመመለስ ጥናት ላይ የተመሰረቱ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በሃገሪቱ ከተጀመረውን የለውጥ ሂደት ጋር ተዳምሮ ውጤቱን ለማፍጠንና ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት የክልሉ መንግስት ህዝብን ያሳተፈ ጥናት በማካሄድ በወሰደው ርምጃም ለሦስት ዞኖችና 44 ወረዳዎች የመዋቀቅር ጥያቄ መመለሱን አስረድተዋል፡፡

በተለይም ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን በውይይት በመፍታት የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ በተፈለገው መስመር ለማስኬድና ከውጤቱም ተቋዳሽ ለመሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

የመዋቅር ጥያቄ መልስ ማግኘቱ ብቻውን ልማት መሆን ስለማይችል የዞኑ ነዋሪዎች ተያይዘው መስራትና ለክልሉም ሆነ ለሃገራዊ ዕድገትና ሰላም የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገነዝበዋል፡፡

ዞኑ በሰባት የገጠር ወረዳና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ ሲሆን በሚቀጥሉ ቀናትም የዞኑ ምክር ቤት ምስረታ፣ ሹመትና የምሁራን የውይይት ጉባኤዎች እንደሚካሄዱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም