በሀገራዊ የለውጥ ጉዞ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል....የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ

119

አዳማ ጥር 24/2011 በተጀመረው ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ፍትህን ለማስፈን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

16ኛው የፌዴራልና የክልሎች ጠቅላይ አቃቤ ህጎች የጋራ የምክክር መድረክ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዋና አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬበመድረኩ መክፈቻ ላይ እንዳሉት በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የፍትህ ስርዓቱ እንዲሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ባላፉት ወራት የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል ወሳኝ የሆኑትን የህግ ማዕቀፎች፣ ተቋማዊ አደረጃጀትና አሰራርን ከመዘርጋት ጀምሮ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

አቶ ብርሃኑ እንዳሉት የፍትህ ዘርፉ በሀገቱ በተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ፣ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት ዕውን እንዲሆን የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።

የዘርፉ አመራሮችና ፈጻሚዎች የለውጡ አካል ሆነው እየሰሩ ቢሆንም አሁንም አመለካከት፣ እውቀት፣ ክህሎትና አደረጃጀት የፍትህ ማነቆ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሁን ያለውን ተልዕኮ በተገቢው መንገድ የተረዳና የሚተገብር፣ በህዝብ ዘንድ አመኔታ ያለው ጠንካራ የፍትህ መዋቅር ለመገንባት የሚያስችል ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።

" አሁን ባለንበት ሀገራዊ ሁኔታ የፍትህ ዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋጥ ጉዳዩ የጎላ ትኩረት የሚሰጠው ነው " ያሉት ዋና አቃቢ ህጉ ፈጣንና ተደራሽነት ያለው አገልግሎትን በማስፋት የተሻለ ሥራ ማከናወን የሚቻልበት አሰራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።

"ለእዚህም አቅም በፈቀደ መልኩ አዳዲስ ቴክኖሎጂን በመዘርጋትና የሰው ኃሉን የማስፈፀም አቅም በማጎልበት የህዝቡን የፍትህ ጥያቄ መመለስ አለብን" ብለዋል።

ባለፉት ወራትየሀገርና የህዝብን ጥቅም አደጋ ላይ የጣሉ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ፣ ህገወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውር ላይ የተሳተፉ፣ ሙስናና የሀገር ሀብት ምዝበራ የፈፀሙ ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ ሥራ በትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል።

የመድረኩ ዓላማ በፌዴራልና በክልሎች መካከል የተቀናጀና ውጤታማ የፍትህ ስርዓት በመፍጠር የለውጡ ዋንኛ አጋዥ እንዲሆኑ ማድረግ መሆኑንም አመልክተዋል።

የይቅርታና ምህረት አሰጣጥ ውጥነት ባለው መልኩ በክልሎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል መድረኩ የጎላ ሚና እንዳለው የገለጹት ደግሞ በጠቅላይ አቃቤ ህግ የይቅርታ ቦርድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘለቀ ደለለውናቸው።

በይቅርታና ምህረት አዋጅ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች በይቅርታ የተፈቱት ባሳዩት ስነምግባርና በፈፀሙት ድርጊት መፀፀታቸውን ከግምት ውስጥ ማስገባት መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሎች የይቅርታ አሰጣጥ የተለያየ መሆኑና በአፈጻጸሙም ክፍተት መታየቱን ጠቁመው በእዚህ ላይ የህግ ማሻሻያዎች ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የጠቅላይ አቃቤ ህጎች ሀገራዊ አደረጃጀትና አሰራር፣ የይቅርታና ምህረት አሰጣጥ፣ የወንጀልና ፍትሃብሔር ጉዳዮች አፈጻጸም፣ የሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባና አደረጃጀት የመረጃ አያያዝ ውጥነት ላይ ያሉ ተሞክሮዎችና ክፍተቶች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም