መገናኛ ብዙሃን ህግን መሰረት አድርገው መስራት አለባቸው- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

56

አዲስ አበባ ጥር 24/2011 መገናኛ ብዙሃን ህግን መሰረት አድርገው እንዲሰሩና ህግ ተላልፈው የተገኙት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።

መገናኛ ብዙሃን ህግን መሰረት ያደረገ ሚዛናዊ መረጃ ለህዝብ ማድርስ ይገባቸዋል እንጂ በህዝቦች መካከል ግጭት የሚፈጥሩ መሆን የለባቸውም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ እንዳሉት መንግስት መገናኛ ብዙሃን ላይ ማስተካከያ ያደርጋል።

በቅድሚያ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ማስተካከያ ይደረጋል፤ በፌዴራልና በክል በየደረጃው ሙያው የሚጠይቀውን መሰረት አድርገው እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል።

በቀጣይ የግል መገናኛ ብዙሃን በጋራ እንዲወያዩ በማድረግ በዘርፉ ያለው ችግር በውይይት ለመፈታት ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።

በግሉም ሆነ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገንቢ ስራ የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው ችግር የሚፈጥሩ ግለሰቦች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲያብብ እና በህዝቦች መካከል መቀራረብ እንዲኖር በሚያስችሉ ስራዎች ላይ መስራት ይገባልም ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን የግለሰቦችን ወይም የቡድኖችን አጀንዳ በመውሰድ በህብረተሰቡ ላይ ችግር መፍጠር የለባቸውም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በህዝቦች መካከል ግጭት ከመፍጠር ይልቅ በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

መገናኛ ብዙሃን ያለባቸውን የገንዘብ ችግር በመቅረፍ የፖለቲካ ነጋዴ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ማገዝ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም