የአዲስ አበባን ወንዞች በማጽዳት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ሊጀመር ነው

57

አዲስ አበባ ጥር 24/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአዲስ አበባን ወንዞች በማጽዳት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ከሶስት ሳምንታት በኋላ ሊጀመር መሆኑን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በአዲስ አበባ መጥፎ ሽታ ያላቸውንና የቆሻሻ መጣያ ወንዞችን በማጽዳት የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከምትስተናግዳቸው ጉባኤዎች በኋላ ይጀመራል።

ከሶስት ሳምንት በኋላ ፕሮጀክቱ እንደሚጀመርና በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ እንደሚደረግበት የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ከአጋር አገሮች ድጋፍ መገኘቱንም ጠቁመዋል።

ወንዞቹን አጽድቶ የቱሪስት መዳረሻ ከማድረግ ባለፈ በወንዞቹ አካባቢ ዋጋቸው ከፍተኛ የሆነ ሪል ስቴቶች እንደሚገነቡም አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ ወደ አዲስ አበባ ቱሪስቶች እንዲመጡ በማድረግ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የሁሉንም የመዲናዋ ነዋሪዎች ድጋፍና ርብርብ እንደሚጠይቅና ለዚህም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም