ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የአገሪቷን ሰላም በሚያደፈርሱ አካላት ላይ መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ ተናገሩ

102

አዲስ አበባ ጥር 24/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያን ሰላም የሚያደፈርሱ አካላት ላይ መንግስት ህግን መሰረት ያደረገ እርምጃ እንደሚወስድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያም በኢትዮጵያ ሰላምና ሉአላዊነት ላይ፣ አንድነቷን ለመከፋፈል የሚፈልጉ አካላት ላይ መንግስት ምንም አይነት ትግስት አይኖረውም ብለዋል።

መንግስት ለሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ብዙዎቹ ዴሞክራሲውን ለመገንባት በብዙ ችገሮች ውስጥ እየሰሩ ቢሆንም ጥቂቶች ግን በንድ በኩል ዴሞክራሲን በሌላ በኩል ደግሞ ግጭትን አማራጭ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ከግጭት ትርፍ የሚፈልጉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለድል እንደማይበቁ አውቀው ይህንን ተግባራቸውን ሊያቆሙ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ከዚህ በኋላ የህዝብን ሰላምና የአገርን ሉአላዊነት በሚያውኩ አካላት ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል።

በዚህ ረገድ እስካሁን ህዝብና መንግስትን የሚሳደቡና የሚተነኩሱ ፓርቲዎችንም ሆነ ግለሰቦችን ተጠያቂ ያላደረግነው ህግ ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን የዴሞክራሲ ጅማሮ ላይ ስለሆንን ነው ሲሉም አክለዋል።

በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀሩ ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው ድል መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ሰላምን ለማወክና ፀረ ዴሞክራሲ የሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል።

በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃሳብ ልዕልና የሚያምኑና ለኢትዮጵያ ሰላም፣ልማት፣ዴሞክራሲና አንድነት የሚሰሩ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም