የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ አፍሪካውያንን እያቀራረበ ያለ ተቋም ለመሆን በቅቷል ተባለ

116

አዲስ አበባ ጥር 23/2011በአፍሪካ ዘመናዊነቱ ግንባር ቀደም እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ አፍሪካውያንን እያቀራረበ ያለ ተቋም ለመሆን በቅቷል ተባለ፡፡

አካዳሚ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የባህል ቀን አክብሯል። 

በጠቅላላው በአሁኑ ወቅት እያሰለጠናቸው ካሉት 1 ሺህ 600 ተማሪዎች መካከል 120ዎቹ የአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ አገራት ዜጎች ናቸው።  

ከኢትዮጵያውያኖች ውጭ ከ19 አገራት የመጡ ተማሪዎች በአካዳሚው ይገኛሉ።

በባህል ቀን አከባበሩ ላይም እነዚሁ የአካዳሚው ሰልጣኞች የተለያዩ የአለባበስ፣ አመጋገብ፣ ዳንስና ሌሎች ትርኢቶችን አቅርበዋል።

ከእነዚህ መካከል የሆነውና በአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሺያንነት ስልጠና እየተከታተለ ያለው ሞዛምቢካዊው ላክሰን ታይሙ የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ አፍሪካውያኖች ከአፍሪካ እንዲማሩ ያደረገ የአፍሪካ የአቪዬሽን ተቋም እንደሆነ ተናግሯል።

ሞዛምቢክ ውስጥ የአቪዬሽን አካዳሚ እንደሌለና ምናልባት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገሬ የአቪዬሽን አካዳሚ ቢገነባ መልካም እንደሆነ ገልጿል።

የባህል ቀኑ መከበሩ የብዙ ባህሎችና ታሪኮች መገኛ የሆነችው አፍሪካ ዜጎቿ እርስ በእርሳቸው ማህበራዊ ትስስር ለመፍጠር ያስችላቸዋል ብሏል።

የአውሮፕላን ጥገና ተማሪው ናይጄሪያዊው ፓትሪክ ዲኬ በበኩሉ አካዳሚው አፍሪካን የመወከል አቅም እንዳለው ገልጿል።

አካዳሚ ከአፍሪካ ምርጥ የሚባለው ነው ከዓለም ጋር ሲነጻጸርም ካሉት ምርጥ አካዳሚዎች ዋንኛው ነው በፍጥነት እያደገ ነው ለሰዎች የምመክራቸው የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ አካል እንዲሆኑ ነው።

የስድስት ወር የስልጠና ጊዜ የቀረው ፓትሪክ የባህል ቀኑ አከባበር ቀጣይነት ባለው መልኩ ቢካሄድ የባህል ልውውጥ በማድረግ ልምድ ለመለዋወጥ ያስችላቸዋል ብሏል።

የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ የሽያጭና የገበያ ልማት ሃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት ተረፈ በበኩላቸው የባህል ቀኑ መከበር አካዳሚው አፍሪካን የሚወክል መሆኑን ለማሳየት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

አካዳሚው አፍሪካውያኖችን አሰልጥኖ ለአፍሪካ አቪዬሽን ጉልህ የሚባል አስተዋጽኦ እያበረከተ ነውም ይላሉ።

አካዳሚው በአሁኑ ወቅት በየአመቱ ከ1 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑንና የአካዳሚውን ተማሪዎች የመቀበል አቅም እ.አ.አ በ2030 ወደ 4 ሺህ ከፍ ለማድረግ መታቀዱንም አመላክተዋል።

ከተመሰረተ 60 ዓመት ያስቆጠረው የአቪዬሽን አካዳሚው ከምስረታው አንስቶ 16 ሺህ 100 ባለሙያዎችን ያስመረቀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ የሚሆኑት ከ48 በላይ አገሮች (አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ) የመጡ ሰልጣኞች ናቸው።

አካዳሚው ተማሪዎችን በአብራሪነት፣ የአውሮፕላን ቴክኒሻንነት፣ በገበያ እና ፋይናንስ እንዲሁም በደንበኞች አገልግሎት መስክ እያሰለጠነ ይገኛል።

የአቪዬሽን አካዳሚው የአብራሪዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት፣ የአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሺያኖች፣ የበረራ አስተናጋጆችና የገበያ ባለሙያዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤቶች አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም