የአገር ውስጥ የገበያ ትስስርን ለማጠናከር የሚረዳ አገር አቀፍ አውደ-ርዕይ ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፈተ

356

አዲስ አበባ  ጥር 23/2011 የአገር ውስጥ የገበያ ትስስርን ለማጠናከር የሚረዳ አገር አቀፍ አውደ-ርዕይ ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፈተ።

የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ባዘጋጀው በዚህ አውደ-ርዕይ ላይ ከሁሉም የአገሪቷ ክልሎች የተውጣጡ 105 ተሳታፊዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው ቀርበዋል።

በአውደ-ርዕዩ አምራቾች የተለያዩ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የአገር ባህል ልብሶችና የተለያዩ አልባሳት፣ የባልትና ውጤቶችና ማር እንዲሁም የተለያዩ ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው ቀርበዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ  በመክፈቻው ስነ-ስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር፣ በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በኩል አምራቾች ለሚያመርቷቸው ምርቶች የገበያ ትስስር መፍጠር አንዱ ዓላማው ነው።

አምራች ኢንዱስትሪዎች እርስ በእርሳቸው የገበያ ትስስር በመፍጠር  የኢኮኖሚ አቅማቸውን  እንዲያሳድጉና  የሸማቹን ህብረተሰብ ግንዛቤ ለማስፋትም የዚህ ዓይነቱ አገር አቀፍ አውደ-ርዕይ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዮሃንስ ድንቃየው በበኩላቸው፣ ለአምራቾች የገበያ ትስስሩን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በውጭ አገር ገበያን ለማፈላለግ፣ በኤግዚቢሽንና ባዘር እንዲሳተፉና የመሸጫ ማዕከላት ግንባታን ለማስፋት እየተሰራ ነው።

በዘርፉ ያለውን ተግዳሮቶች ለመፍታትና ተወዳዳሪ የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለማፍራትም ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችል አዋጅ ተዘጋጅቶ ለማጸደቅ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የዐውደ-ርዕዩ ተሳታፊዎችም የዚህ ዓይነቱ አውደ-ርዕይ ላይ መሳተፋቸው የገበያ ትስስሩን ለመፍጠርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የተሻለ አማረጭ እንደሚፈጥርላቸው ይናገራሉ።

ከኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማራችው ፍቅርተ ክብሩ እንደምትለው፣  በቤተሰብ የጀመሩት ይህ ስራ በ2008 ዓ.ም ወደ ስራ የገቡበት መነሻ ገንዘብ 5 ሺህ ብር ነበር።

አሁን መካከለኛ አምራች ወደሚለው ተሻግረው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ካፒታል ላይ መድረሳቸውን ገልጻ፣ ይህም በባልስጣኑ በተለያዩ ጊዜያት ባመቻቹላቸው የገበያ ትስስርና ድጋፍ የመጣ መሆኑን ትናገራለች።

ከአማራ ክልል ተሳታፊ የሆነችው ወይዘሪት ቤተልሄም ግርማ ደግሞ የማር ምርት ይዛ የቀረበች ሲሆን በ2010 ዓ.ም ወደ ስራው እንደገባች ገልጻለች።

በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ ባዛሮችና አውደ-ርዕዮች ተሳታፊ በመሆኗ በአደስ አበባ ሁለት ቦታዎች በሳሊተ ምህረትና በጃክሮስ ቅርንጫፍ በመክፈት የገበያ ዕድሏን እንዳሰፋችና በካፒታልም ደህና ውጤት ያስመዘገበች መሆኑን ገልጻለች።

በአውደ ርዕዩ ከመላው አገሪቷ የተውጣጡ 85 አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች፣ 12 ከተለያዩ አጋር አካላት የተውጣጡ ተሳታፊዎችና 8 የዘርፉ የልማት ተቋማት እንደተሳተፉ ተገልጿል።

በተያዘው በጀት ዓመት 17 ሺህ 946 ለሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና 14 ሺህ 61 ኢንዱስትሪዎች የግንዛቤ መስጨበጫ ስልጠናዎች መደረጋቸውንም የባለስልጣኑ መረጃ ያሳያል።

በዚህ ዓመትም 2 ሺህ 741 አዳዲስና ነባር ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋምና ማጠናከር እንዲሁም ለ31 ሺህ 346 ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠር እንደተቻለም ተገልጿል።

ዐውደ-ርዕዩ ”የተቀናጀ የገበያና ግብይት ድጋፍ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ውጤታማነት” በሚል መሪ ሐሳብ ከጥር 23 አስከ ጥር 30 የሚቆይ ሲሆን በ20 ሺህ ሰዎች እንደሚጎበኝና የ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተካሄደ እደሆነም ተጠቁሟል።