በአገሪቱ ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሴቶች በኢኮኖሚ መስኮች ተሰማርተው ተጠቃሚ ሆነዋል

57

አዳማ ጥር 23/2011 በአገረቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በሚያስገኙ መስኮች መሰማራታቸውን የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የዘርፉ ተቋማት በተገኙበት የግማሽ ዓመት አፈጻጸሙን ዛሬ በቢሾፍቱ መገምገም ጀምሯል።

በሚኒስቴሩ የስትራቴጂያዊ ሥራ አመራር ተወካይ አቶ በሽር ሳልህ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት በግማሽ ዓመቱ ሴቶቹ  በተለያዩ መስኮች በመሰማራት ተጠቃሚ ሆነዋል።

ሴቶቹ ተጠቃሚ የሆኑት በጥቃቅንና አነስተኛ፣በራስ አገዝ፣ በኅብረት ሥራ ማህበራት፣ በግብርናና ሌሎች መስኮች ተደራጅተው ነው ብለዋል።

ሥራውን ለማካሄድ እንዲያስችላቸውም 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብድር መሰጠቱን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ መቆጠባቸውን ተወካዩ አስረድተዋል።

በሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጄንሲዎች ፣ በግብርና ፣ ትምህርትና ጤና ላይ በሴክተር ተቋማት የታየው ቅንጅታዊ አሰራር በዘርፉ ለተገኘው ውጤት ቁልፍ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል።

የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር የተሻለ ውጤት ቢገኝም ፤ በህፃናትና ወጣቶች ዙሪያ አሁንም በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የመረጃ አያያዝ ክፍተት፣ከክልሎች የሚመጡ ሪፖርቶች ግልፅነት ጉድለት፣ሥራዎችን ቆጥሮ መስጠትና መቀበል ላይ ያለው ማነቆዎች ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን ተወካዩ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በማሳደግ ረገድ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የእቅድ ዝግጅት ክትትል ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ዓለሙ ናቸው።

በግብርና፣ በጥቃቅንና አነስተኛ፣በቁጠባና ብድር አገልግሎትና በኅብረት ሥራ ማህበራት ከ400ሺህ በላይ ሴቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በክልሉ ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት በመስጠት ከ218 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴቶች መጠቀማቸውን ተናግረዋል።

የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ የአለምፀጋ አስፋው በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት በአገር ደረጃ የሴቶችን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በሴቶችና ህፃናት ላይ ሲደርሱ የነበሩ ፆታዊ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መቀነሳቸው፣በተለያዩ የገቢ ማስገኛ አማራጮች ተሰማርተው ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለማላቀቅ የተሰሩ ሥራዎች የተሻለ አፈፃፀም ታይቷል ብለዋል።

በተመሳሳይ ሴቶች የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር አግኝተው ከሀብቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም