በአማራ ክልል በምርት ዘመን ጥቅም ላይ የሚውል 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እየተጓጓዘ ነው

100

ባህር ዳር ጥር 23/2011 በአማራ ክልል ለ2011/12 ምርት ዘመን ጥቅም ላይ የሚውል 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ እየተጓጓዘ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በምርት ዘመኑ ከ5 ነጥብ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለማሰራጨት ታቅዷል።

የቢሮው የግብርና ግብዓቶችና ገጠር ፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ተስፋ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ  ጥቅም ላይ ከሚውለው ማዳበሪያ እስካሁን ከ818 ሺህ ኩንታል ወደ ክልሉ ደርሷል።

በመኽር ወቅት አዝመራ ጥውም ላይ የሚውለው ማዳበሪያ ወደ 23 ዩኒየኖች ማዕከላዊ መጋዝኖች እየተጓጓዘ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒየኖቹ ማዳበሪያ ከመጋዘኖቹ ለኅብረት ሥራ ማህበራት ለማሰራጨት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በዚህ ዓመት  ወደ ክልሉ የሚገባው ማዳበሪያ መጠን በቀዳሚው ዓመት ገብቶ ጥቅም ላይ ከዋለው ጋር ሲነፃፀር በ278 ሺህ ኩንታል ያህል ብልጫ እንዳለውም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

እስከ ግንቦት ወር ተጠቃሎ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ማዳበሪያ የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሠረት አድርጎ በተሰበሰበ መረጃ አማካይነት መሆኑንም አስረድተዋል።

በአዊ ዞን የአድማስ ዩኒየን የግብይት ኃላፊ አቶ መሰረት ብርሃኑ ማዳበሪያውን ለማከማቸት በአንድ ጊዜ 150 ሺህ ኩንታል የሚይዙ ደረጃቸውን የጠበቁ ሶስት መጋዘኖች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የመርከብ ዩኒየን የግብዓት ኃላፊ አቶ ተመስገን አበበ በበኩላቸው 170 ሺህ ኩንታል የሚይዙ ሁለት መጋዘኖች ማዳበሪያውን ለመቀበል እየተጠባበቁ ነው ብለዋል።

ማዳበሪያው ሳይቆራረጥ ወደ አርሶ አደሩ በማድረስም የዘመኑ ግብርና ሥራ በወቅቱ እንዲከናወን ድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ማዳበሪያው ወደ ክልሉ እየገባ ያለው በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አማካይነት እንደሆነም ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም