የአዘዞ -ጎንደር ኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

115

ጎንደር ጥር 22/2011 በወሰን ማስከበር ችግር ግንባታው የተጓተተውን የአዘዞ- ጎንደር የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን ተቋራጩ ድርጅት አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ በሦስት ዓመታት ጊዜ ለማጠናቀቅ ታስቦ ግንባታው የተጀመረው አምና ነበር።

የራማ ኮንስትራክሽን ተቋራጭ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት ግንባታው የተጓተተውን የ12 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ለአገልግሎት ለማብቃት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።

ከአጠቃላይ የመንገዱ ርዝመት 10 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጎለት በአዲስ መልክ የሚሰራ ሲሆን ፣ቀሪው መለስተኛ ማሻሻያ እንደሚደረግለት አስረድተዋል።

የመንገዱ ስፋት ከሰባት ሜትር ወደ 30 ሜትር እንዲያድግ መደረጉን ያስረዱት ሥራ አስኪያጁ፣መንገዱ በሁለቱም አቅጣጫዎች ስድስት ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ  በሚያስተናግድበት ሁኔታ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

መንገዱ ለቀጣይ 20 ዓመታት ሊኖር የሚችለውን የትራፊክ እድገት ታሳቢ በማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የጎንደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ እርዚቅ ኢሳ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ለአገልግሎት እንዲበቃ ከተቋራጩ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንገድ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኅብረተሰቡን ቅሬታ ከመፍታቱም በላይ፤ ከተማዋን ለቱሪዝም ምቹ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ እየተከናወነ ያለው ፌዴራል መንግሥት በመደበው 881 ሚሊዮን ብር በጀት ሲሆን፣በ2013 ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ  ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም