ባህላዊ የምክክር መድረኩ ለአካባቢው ሰላም አስተዋጽኦ አበርክቷል-ርዕሰ መስተዳደር ሚሊዮን

85

ሀዋሳ ጥር 22/2011 የሲዳማ የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች የጀመሩት ባህላዊ የምክክር መድረክ ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ፡፡

የሲዳማ የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች "ሃላሌ" የተሰኘ ባህላዊ የምክክር መድረክ በይርጋለም ከተማ አካሂደዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ እንደገለጹት መድረኩ ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ አስተዋጽኦው የጎላ ነው።

"ባህላዊ የምክክር መድረኩ የሲዳማ ሽማግሌዎችን የመደማመጥ ትውፊት የሚያሳይ ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ መድረኩ የሲዳማ የክልል ጥያቄ አፈጻጸም ሂደትና የወጣቱን የትግል አካሄድ ተከትሎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

መድረኩ የወጣቶችን ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ከአገር ሽማግሌዎች መካከል ከዎንሾ ወረዳ የመጡት አቶ ከበደ በጠና እንደገለጹት ዓመታትን ያስቆጠረ የክልል ጥያቄዎች ሕገ መንግሥታዊ  ምላሽ እንዲያገኝ ጠይቀዋል።

ለዚህም ወጣቱን የመምከርና በባህላዊ መንገድ የማስተማር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል።

ከይርጋለም የመጡት የአገር ሽማግሌ አቶ መኮንን ቡዋኔ በበኩላቸው ወጣቱ ጥያቄውን በሽማግሌዎች ምክር እየታገዘ በሰላማዊ መንገድ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ወጣት አበበ አርጊሶ "ሃላሌ" የተሰኘው ባህላዊ ሥርዓት ወጣቶች የሚያከናውኗቸውም ማንኛውም ጉዳዮች ከሽማግሌዎች ይሁንታ የሚያገኝበትና ካጠፋም የሚታረምበት መሆኑን ተናግሯል፡፡

"የምክክር መድረኩ ጥያቄያችንን በሰላማዊ መንገድ ለማስቀጠልና ከሌሎች ጋር እንዴት መኖር እንዳለብን ምክር የወሰድንበት ነው" ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም