የጀመርነውን የደም ልገሳ አጠናክረን እንቀጥላለን ....በጋምቤላ ደም ለጋሾች

71

ጋምቤላ ጥር 22/2011 በጋምቤላ ክልል በደም እጦት ምክንያት የሚሞቱ ዜጎችን ለመታደግ የጀመሩትን የደም ልገሳ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ደም ሲለግሱ የተገኙ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡

የክልሉ ደም ባንክ በበኩሉ የለጋሾችን ቁጥር በማሳደግ የደም አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጿል፡፡

የጤናማ እናትነትን ወር አስመልክተው ደም ሲለግሱ የነበሩ አንዳንድ የክልሉ ነዋሪዎች እንዳሉት በደም እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን የሰው ሞት ለመታደግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

ደም ሲለግሱ ካገኘናቸው ነዋሪዎች መካከል ፓስተር መኮንን እንኮሳ እንዳሉት በተለያዩ ምክንያቶች ለተጎዱ ዜጎች ደም መስጠት በሃይማኖታዊ አስተምህሮም ቢሆን የሚደገፍ በመሆኑ ደምል ለመለገስ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

የጀመሩትን የደም ልገሳ ወደፊትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው በደም እጦት ምክንያት በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሞት ለመታደግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አማካሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኩዊች ዊው በሰጡት አስተያየት በክልሉ በደም እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን ሞት ለመከላከል ደም በመለገሳቸው የድርሻቸውን በመወጣታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የአመራር አካላት ህብረተሰቡን ከማወያየት ባለፈ ደም በመለገስ ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን መስራት አለብን ብለዋል።

የኑዌር ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሉዋል ዶስ በበኩላቸው በዞኑ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የሚደርስባቸው ዜጎች በደም እጥረት ምክንያት ለሞት የሚጋለጡበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው ይህንን ለመታደግ የሚለግሱትን ደም በማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ራሳቸው ደም ከመለገስ ባለፈ ሌሎች እንዲለግሱ ግንዛቤ ለማሳደግና ለማስተማር ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ደም መለገስ የሌሎችን ሕይወት ከመታደግ ባለፈ ለራስ ጤንነት አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ከፑኝዶ ሆስፒታል የመጡት ዶክተር አብዱር አዛክ ናቸው፡፡

ለ12ኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውን የተናገሩት ዶክተሩ በእዚህም ምንም የጤና ችግር እንዳልገጠማቸውና ደም መለገስ ለታማሚውም ጭምር ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም የጀመሩትን የደም ልገሳ አጠናክረው  እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት።

የጋምቤላ ጠቅላላ ሆስፒታል ሜድካል ዳይሬክተር ተወካይ ዶክተር ኡማን ኡጉድ በበኩላቸው በሆስፒታሉ ያለው የደም አቅርቦት ቀደም ሲል ከነበረው እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም የሆስፒታሉን የደም ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ለማሟላት ከክልሉ ደም ባንክ ጋር ያላቸውን ቅንጅታዊ ሥራ በማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ደም ባንክ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኡጁሉ ኡጋላ በበኩላቸው በደም እጦት ምክንያት የሚከሰተውን የዜጎች ሞት ለመታደግ ዘንድሮ 1ሺህ 500 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ቢታቀድም እስካሁን ማሳካት የተቻለው 350 ዩኒት ደም ብቻ ነው።

በክልሉ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በእቅዱ መሰረት ደም ለመሰብሰብ እንቅፋት መሆኑንም ገልጸው፣ የተሰበሰበው ደም ለጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል መላኩን አስረድተዋል።  

የደም ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመስራት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የሚሰበሰበውን የደም መጠን ለማሳደግ በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ ህዝባዊ መድረኮች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሰራቱን ገልጸው፣ በቀጣይ በጋምቤላ ጠቅላላ ሆስፒታል በተለያዩ መድረኮች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደሚጠናከር ገልጸዋል።

ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራረን በማስፋት የሆስፒታሉን የደም ፋላጎት ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም