ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር የመቀላቀል ሕገ-ወጥ ተግባርን ለመከላከል መገናኛ ብዙኃን ድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

93

አዳማ ጥር 21/2011ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር የመቀላቀል ሕገ-ወጥ ተግባርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የመገናኛ ብዙኃን ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮዽያ የመድኃኒት፣ የምግብና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ባለሥልጣን ጠየቀ።

በጉዳዩ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን አካላት የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ እንዳስታወቁት ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል እየተፈጸሙ ያሉት ሕገ ወጥ ተግባራት እየተስፋፉና አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል።

በተለይ እንጀራ፣ በርበሬ፣ ማርና ቅቤን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል  በኅብረተሰቡ ጤና  ጉዳት እየደረሰ መሆኑን አስረድተዋል።

ድርጊቱ በድብቅና በረቀቀ መንገድ እንደሚፈጸም የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ድርጊቱን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የመገናኛ ብዙኃን  በጉዳዩ ላይ አጀንዳ በመቅረጽ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል።

በባለሥልጣኑ የፕሮጀክትና ፕላን ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ወይዘሮ አለም እሸቴ በበኩላቸው በአገሪቱ ከ132 ሺህ በላይ ምግብ አምራች፣ አስመጪ፣ ላኪ አከፋፋይ፣ ቸርቻሪ ፣ ሆቴሎችና የመንገድ ዳር ላይ ምግብ የሚዘጋጁ ተቋማት እንዳሉ አስታውቀዋል።

ተቋማቱን በባለስልጣኑ አቅም ብቻ መቆጣጠር ስለማይቻል መገናኛ ብዙኃን በሙያቸው እገዛ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ የቁጥጥር ሥራውን ለማጠናከር በዚህ ዓመት አዲስ አበባን ጨምሮ በሞያሌ፣ ቶጎ ውጫሌ፣ ጅማና ደሴ ከተሞች በተመረጡ 37 ቦታዎች ቅኝትና ጥናት እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሶስት ቀናት በሚቀየው መድረክ ላይ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተወጣጡ ጋዜጠኞችና የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም