የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመለካከት ለውጥ ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ተጠቆመ

97

ወልዲያ ጥር 21/2011 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአመለካከት ለውጥ ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር አመለከቱ።

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች፣ከሰሜን ወሎና ከዋግኸምራ ዞኖች አመራሮችና የወጣቶች  አደረጃጀቶች ተወካዮች የተካፈሉበት መድረክ ትናንት  ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ  በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ተቋማቱ ከተቋቋሙበት ዓላማ አንጻር የአመለካከት ለውጥ  በማምጣት ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

በተቋማቱ ላይ የሚሰራው የአመለካከት ለውጥ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ አዎንታዊ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲ እንደ ስሙ ዩኒቨርሳል (ዓለም  አቀፍ) ስለሆነ የሚጠበቅበት ኃላፊነትም ሁሉን አቀፍ ዕውቀት ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ እንዲሁም  የማህበረሰቡን ችግሮች መፍታት መሆኑን ምሁሩ አብራርተዋል።

ወጣቱ ትውልድ በራሱ የሚተማመን፣ ሚዛናዊ፣ ለአገሩና ለህዝቡ የሚቆረቆር አድርጎ መቅረጽ እንደሚያስፈልግም ዶክተር ዳኛቸው ተናግረዋል።

የወልዲያ ወጣቶችን የወከለው ወጣት ጌታቸው ፋሲካው ወጣቱ ትውልድ ካለፈው ትውልድ የአገር ፍቅርን በመውረስ ጉድለት እንደሚታይበት ይናገራል።

"አባት እናቶቻችን የጸና የኢትዮጵያዊነት እምነትና ፍቅር አላቸው።በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ላይ የምንገኝ ወጣቶች የእናት አባቶቻችን ያህል እምነት የለም'' ብሏል።

ወጣቱ የአገሪቱን እድገትና ለውጥ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሁኔታ ባገናዘበ መንገድ ከምሁሩ  ጋር የተደረገው ውይይት ጠቃሚ ግንዛቤ እንደጨበጠበት ገልጿል።

የወልዲያ ዩኒቨርስቲ መምህሩ አቶ አጥናፍ በዙ በበኩላቸው በአገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚስተዋሉትን ግጭቶች ለማስቆም በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል።

በውይይቱ ዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች፣ከሰሜን ወሎና ከዋግኸምራ ዞኖች የተወጣጡ  አመራሮችና የወጣቶች አደረጃጀቶች ተወካዮችና እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም