የማህበረሰብ አገልግሎቱን በማጠናከር ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እተጋለሁ --የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ

66

ሐዋሳ ጥር 21/2011 የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎቱን በማጠናከር ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ  እንደሚሰራ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ በሚያከናውናቸው ምርምሮችና በማህበራዊ አገልግሎት ዙሪያ ከኅብረተሰቡ ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።

የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሐብታሙ አበበ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው አገልግሎቱን በማጎልበት ኅብረተሰቡን በጥናትና ምርምር ሥራዎቹ ተጠቃሚ እንዲሆን ይሰራል።

ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ የሚያከናውናቸው ምርምሮች በመጠጥ ውሃ፣ በግብርናና በትምህርት መስኮች ላይ እንደሚያተኩሩና የሕዝቡን መሠረታዊ ችግሮች ይፈታሉ ተብለው እንደሚጠበቁም  ገልጸዋል።

በሥራ ፈጠራ፣ በማጠናከሪያ ትምህርት በግብርናው መስኮች በመሥራት ላይ እንደሚገኝም  አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ ይህን የሚያከናውነው የማህበረሰብ አገልግሎት እምብዛም ስለማይታወቅ ከኅብረተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር መድረኩ መዘጋጀቱን ዶክተር ሐብታሙ አመልክተዋል።

የሐዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አያሌው ዝና በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ በቂ ግንዛቤ ባለመፈጠሩ ከማህበረሰቡና ከዞኑ አስተዳደር ክፍተት መፍጠሩን  በዚህም አገልግሎቱን  ለማገዝ ሳይቻል መቆየቱን ይናገራሉ።

ዩኒቨርሲቲው የሆሳዕና ከተማ በማስተር ፕላን እንድትመራ ለሚያከናውነው ሥራ በሚቀጥለው በጀት ዓመት 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የአምብቾ ጎዴ ቀበሌ አባገዳ በቀለ ጅራ እንዳሉት በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ከዚህ በፊት ተወያይተውም ሆነ ተሳትፈው እንደማያውቁ  ገልጸው፣ ዘንድሮ የተጀመረው ውይይት ችግሮቻቸውን ለማሳወቅና ለመመካከር  አስችሎናል ብለዋል።

መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት የመጡት አቶ ዳኛቸው ዓለሙ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲ ከምስረታው ከ2004 ጀምሮ የሚያከናውናቸው የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች አመርቂ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ታምራት ፍቅሬ የሆሳዕና ከተማ ዕድገት ማስተር ፕላኗን በጠበቀ መልኩ ለማከናወን  ፕሮጀክት መቀረጹን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በከተማዋ የሚካሄደው ሕገ ወጥ ግንባታን ለመቆጣጠር  እንደሚያስችልም እምነታቸውን ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ስርጸት ጉዳዮች ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጸደቀ ላምቦሬ ዩኒቨርሲቲው ለሐዲያ ዞን አርሶ አደሮች የተሻሻለና ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ የስንዴ ዘር፣ ለደጋማ አካባቢዎች  ደግሞ የአፕል ችግኞች እንዲሁም ቡና በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ ተናግረዋል።

አርሶ አደር መልሰው ሐሲቦ ከስድስት ዓመታት በፊት በዩኒቨርሲቲው የቀረበላቸውን አፕል በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ።በዓመት ሁለት ጊዜ ምርቱን በመሰብሰብ እስከ አራት ሺህ ብር እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም