ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድና  በፈጠራ ስራ ተጠቃሚ ሆነናል… የቴክኒክና ሙያ  ኮሌጅ ምሩቃን

101
ግንቦት 19/2010 ባለፉት አመታት ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድና የራሳቸውን ፈጠራ በማበልጸግ ተጠቃሚ መሆናቸውን  ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች የተመረቁ   ወጣቶች ገለጹ ፡፡ ወጣት አምሀ ወንድሙ በተግባረ ዕድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በብረታብረት ስራ ለ3 ዓመታት ሰልጥኖ በ2006 ዓ.ም ተመርቋል፡፡ ከሶስት  የስራ አጋሮቹ ጋር ተደራጅቶ በ30 ሺህ ብር ካፒታል  “ቢ ኤም ደብሊው” የተሰኘ የብረታብረት  ኢንጂነሪንግ ማህበር መስርተው የብረት መቁረጫና መበየጃ ማሽኖችን በመስራት  የጀመሩት ስራ ውጤታማ ሆኖላቸዋል፡፡ ወጣት አምሃ የሚመራው ማህበር  ሀገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታስገባቸውን የግንባታና የመኪና መለዋወጫ እቃዎችን በሀገር ውስጥ ያመርታል፡፡ ማህበሩ ከሚያመርታቸው ማሽነሪዎች ውስጥ ጠጠር  ማምረቻ ( ክሪቸር)፣ የአርማታ መቀላቀያ (ሚክሰር) ፣ ትላልቅ እቃዎችን ከመኪና ላይ ማውርጃና መጫኛ (ሊፍተር)፣ የቡና መቁያ ማሽን፣  የከባድ መኪኖች  መለዋወጫ( ስፔር ፓርቶች) ዋና ዋናዎቹ  ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በበርካታ ሰዎች የሚንቀሳቀስን የሽመና መሳሪያ  በማሻሻል በአንድ ሰው  በቀላሉ  መስራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ  ሰርተው ለገበያ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን  ወጣት አምሀ ተናግሯል፡፡ በቀጣይ ደግሞ በሙያቸው ከውጭ የሚመጡ  ቀለል ያሉ የግንባታ  ማሽነሪዎችን በስፋት ለማምረት እና ወደ ፋብሪካ ደረጃ ለማሳደግ እየሰሩ እንደሚገኙም ነው ወጣቱ ያብራራው፡፡ ማህበሩ ለ13 ወጣቶች ቋሚ የስራ እድል ከመፍጠሩም በላይ የመስሪያ ካፒታሉንም ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ አድርሷል፡፡ ወጣት ካሳሁን ወዳጆ በማህበሩ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ እንዳለው በሚያገኘው ገቢ ህይወቱን በአግባቡ መምራት ችሏል፤ ሙያውን ለማሻሻልም  እድል ፈጥሮለታል፡፡ ወጣት ዘካርያስ አምሀም ማህበሩ ውስጥ በብየዳ ስራ ተቀጥሮ መስራት ጀምሮ አሁን በራሱ ፈጠራ አዲስ ማሽን ለመስራት ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ሌላው ከተግባረ እድ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በእንጨትና ብረታ ብረት ዘርፍ የተመረቀው ታሪኩ ከበደ እንዳለው ትላልቅ ግንዶችን በቀላሉ  መሰንጠቅ የሚያስችል የእንጨት መሰንጠቂያ፣  ቅርጽ ማውጫ ማሽነሪዎችን፣ የቢሮ ጠረጴዛዎችንና መቀመጫዎችን   ሰርቶ  ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ ከውጭ የሚገባውን የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽን  የሚተካ  የእንጨት መሰንጠቂያ  መስራት በመቻሉ በ2009 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ  በተደረገ  ውድድር ተሸላሚ መሆኑንም  ነው የገለጸው፡፡፡ ወጣት ታሪኩ እንዳብራራው ከሶስት ዓመታት በፊት ከ15 ሺህ ባልበለጠ መነሻ ካፒታል የተጀመረው ስራ  በአሁኑ ወቅት ካፒታሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ  አድጓል፡፡ ማህበሩ ለ5 ሰዎች ቋሚ የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን የችፑድ ማምረቻ ማሽን ሰርቶ   ከእንጨት ፍቅፋቂ የችፑድ ምርት በስፋት አምርቶ  ለገበያ ለማቅርብ እየተጋ እንደሚገኝም ተናግሯል፡፡ ወጣቱ ለሰራው ቴክኖሎጂ ከመንግስት በኩል የተሰጠው እውቅና፣ የፈጠራ ባለቤትነት መብትና የመስሪያ ሼድ ድጋፍ ስራው ን ውጤታማ እንዳደረገለትም ነው ወጣቱ ያብራራው፡፡ በአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የስራ እድል  ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ ግርማ ተስፋይ መንግስት በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችን የዘርፉ ምሩቃን ተደራጅተው ወደ ገንዘብ እንዲለውጧቸው እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ባለፉት አመታት በቴክኒክና  ሙያ ኮሌጆች የተሰሩ 85 ቴክኖሎጂዎችን ለ469 ኢንተርፕራይዞችና የቴክኒክና ሞያ ምሩቃን መተላለፋቸውን  አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም