ኢትዮጵያ በምታካሂደው ሁለንተናዊ ለውጥ የጀርመን ድጋፍ አይለያትም - ፕሬዚዳንት ፍራንክ ሽተንማዬር

130

አዲስ አበባ ጥር 21/2011 ኢትዮጵያ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በምታከናውነው ለውጥ የጀርመን ድጋፍ እንደማይለያት የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዎልተር ሽተንማዬር ገለጹ።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህልወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው "ኢትዮጵያና ጀርመን ያላቸውን ታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ዘርፈ ብዙ አጋርነት ማሸጋጋር አለባቸው" ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ለሚገኙት የጀርመን ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዎልተር ሽታንማዬር ትናንት በብሔራዊ ቤተመንግስት የራት ግብዣ አድርገዋል።

በስነስርዓቱም የጀርመን ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብን ጨምሮ ከኢትዮጵያ በኩል የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና አርቲስቶች ተገኝተዋል።

"የኢትዮጵያ የቅርብ ወራቶች ታሪክ ለመለወጥ ፍላጎትና ድፍረት ካለ ምንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው"

የጀርመኑ ፕሬዚዳንት
ፍራንክ ዎልተር ሽተንማዬር

ፕሬዚዳንት ሽታንማዬር በዚህ ወቅት "የኢትዮጵያ የቅርብ ወራቶች ታሪክ ለመለወጥ ፍላጎትና ድፍረት ካለ ምንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን ለውጥ ጀርመን በልዩ ትኩረት እየተከታተለችው መሆኗል ተናግረው፤ ለውጡ በአገሪቱ የዳበረ ማህበራዊ ተሳትፎና ዴሞክራሲ እንደሚያሰፍን እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን ለማረጋጋት ቁልፍ ሚና እየተጫወተች መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሽታንማዬር፤ "በኢትዮጵያና ኤርትራ የተፈጠረው ሰላም ከቀጣናው ባለፈ በአህጉሩ ተስፋን ያበሰረ ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ እያከናወነችው ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ጀርመን እንደምትደግፈው ጠቁመዋል።h

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጀርመን ረጅም ጊዜ የቆየውን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

"ካለንበት ፈጣን ለውጥ አንጻር ኢትዮጵያን የመጎብኛ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው"

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በሁለቱ አገሮች መካካል ዘርፈ ብዙ አጋርነት ለመፍጠር ቁልፍ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቷ "ካለንበት ፈጣን ለውጥ አንጻር ኢትዮጵያን የመጎብኛ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው" ሲሉ ለሌሎች አገሮችም ጥሪ አቅርበዋል።

ከወዳጅ አገሮች ጋር የሚኖረው ግንኙነት በተለመደው መንገድ የሚሄድ ሳይሆን በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ በሚደግፍ መልኩ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የጀርመን የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ለመሰማራት እያሳየ ያለው ፍላጎት የሁለቱ አገሮችን የንግድ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጎለብተውም ፕሬዚዳንቷ አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በአውሮፓ ካሏት ዋነኛ የንግድ መዳረሻ አገሮች መካካል ጀርመን አንዷ ስትሆን፤በሁለቱ መካከል ያለው ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ ከሶስት መቶ ሚሊዮን ዩሮ በላይ መድረሱን የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ኢትዮጵያ በዋናነት ቡና፣ የቅባት እህሎችንና የአበባ ምርቶችን ወደ ጀርመን ስትልክ፤ ማሽነሪዎችን፣ የቴክኖሎጂ ምርቶችንና የአውሮፕላን መለዋወጫ ዕቃዎች ከጀርመን ታስገባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም