በምዕራብ ወለጋ ዞን በፀጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ 947 ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ሥራ ጀመሩ

70

ነቀምቴ ጥር 20/2011 በምዕራብ ወለጋ ዞን በፀጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ 947 ትምህርት ቤቶች ሥራ መጀመራቸውን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሥራ አሰኪያጅ አቶ ሙላቱ ዲባ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በዞኑ በፀጥታ ችግር ለሁለት ሳምንታት ተዘግተው የነበሩት የአንደኛ፣ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች  አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

በዞኑ አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ የተከፈቱት ትምህርት ቤቶች በ20 የገጠር ወረዳዎችና በሶስት ከተሞች እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በጊምቢ ፣በላሎ አሳቢ፣ ቤጊናና ሌሎች ወረዳዎች ማስተማር ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶችን ሥራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ትምሀርት በተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች የሚገኙ መምህራን ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የባከነ የትምህርት ክፍለ ጊዜን ለማካካስ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ የላሎ አሳቢ ወረዳ የእናንጎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ነጋ በቀለ በሰጡት አስተያየት የባከኑትን የትምህርት ክፍለ ጊዜ ለማካካስ ሙሉ ቀንና የእረፍት ጊዜን በመጠቀም ትምህርት እየተሰጠ ነው።

እሳቸውን ጨምሮ የትምህርት ቤቱ መምህራንና ተማሪዎችም በሙሉ ፍላጎት በማካካሻ ፕሮግራሙ እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።

የቤጊ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት ሱፐርቫይዘር አቶ ፍሮምሣ ወጋሪ በዞኑ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ካጋጠማቸው አካባቢዎች መካከል ወረዳዋ አንዷ በመሆኗ የመማር ማስተማር ሂደት ተስተጓጎሎ መቆየቱን ገልጸዋል።

አሁን የተገኘውን ሰላም በመጠቀም የባከነውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በዞኑ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በ995 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደት ተቋርጦ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም