በካናዳ ኦቶዋ ማራቶን አትሌት ገለቴ ቡርቃና አትሌት የማነ ጸጋይ አሸነፉ

73
አዲስ አበባ ግንቦት 19/2010 ዛሬ በካናዳ ኦቶዋ የማራቶን ውድድር አትሌት ገለቴ ቡርቃና አትሌት የማነ ጸጋይ አሸነፉ። በሴቶች ውድድር አትሌት ገለቴ ቡርቃ 2 ሰአት ከ22 ደቂቃ ከ17 ሴኮንድ አሸናፊ ስትሆን የገባችበት ጊዜ በካናዳ በሴቶች በሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮች ከተመዘገቡ ሰአቶች ፈጣኑ ሆኖ ተመዝግቧል። የ32 ዓመቷ አትሌት ጥር 17 ቀን 2010 ዓ.ም በዱባይ ማራቶን 2 ሰአት ከ20 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ ያስመዘገበችው ጊዜ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቷ ነው። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሕይወት ገብረኪዳን 2 ሰአት ከ26 ደቂቃ ከ11 ሴኮንድ ሁለተኛ የወጣች ሲሆን ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። አሜሪካዊቷ ሳራ ሆል 2 ሰአት ከ26 ደቂቃ ከ20 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። በወንዶች ኢትዮጵያዊው አትሌት የማነ ጸጋይ 2 ሰአት ከ8 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ አሸናፊ ሆኗል። እ.ኤ.አ በ2014 በራሱ ተይዞ የነበረውን የቦታውን ክብረወሰን 2 ሰአት ከ6 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ ለማሻሻል እንደሚሮጥ ከውድድሩ በፊት ቢገልጽም ያንን ማሳካት ሳይችል ቀርቷል። አትሌት የማነ እስከ መጨረሻዎቹ ሁለት ኪሎ ሜትሮች ሲመራ የነበረውን ኬንያዊውን ጆን ኮሪርን ከኋላው ደርሶ በመቅደም ነው አንደኛ መውጣት የቻለው። እ.ኤ.አ በ2014 በሮተርዳም ማራቶን 2ሰአት ከ4 ደቂቃ ከ48 ሴኮንድ የገባበት ጊዜ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቱ ሆኖ ተመዝግቦለታል። ኬንያዊው ጆን ኮሪር 2 ሰአት ከ9 ደቂቃ ከ14 ሴኮንድ ሁለተኛ ሲወጣ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አዱኛ ታከለ 2ሰአት ከ9 ደቂቃ ከ26 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። አትሌት ገለቴ ቡርቃና አትሌት የማነ ጸጋይ ውድድሩን በማሸነፋቸው እያንዳንዳቸው የ40 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የተሸለሙ ሲሆን በሁለቱም ጾታዎች ሁለተኛና ሶስተኛ የወጡ አትሌቶች በቅደም ተከተል የ20 እና 10 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በአጠቃላይ በሁለቱም ጾታዎች ከአንድ እስከ አስር ለወጡት አትሌቶች የ152 ሺህ ዶላር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ዘንድሮ ለ44ኛ ጊዜ የተካሄደው የኦቶዋ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም