የማንኩሽ መጠጥ ውሃ በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት በቃ

102

አሶሳ ጥር 20/2011 በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በማንኩሽ ከተማ በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው  የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ።

ፕሮጀከቱ የከተማውንና አካባቢው 20 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመታት የፈጀ ሲሆን፣ግማሽ ሚሊዮን ሊትር ውሃ ማጠራቀሚያና በርካታ ቦኖዎችም ተዘርግተውለታል።

ፕሮጀክቱ ከከተማው 25 ኪሎ ሜትር ላይ ከተቆፈረ ጥልቅ ጉድጓድ ከሚመነጭ ውሃ  በመሳብ ጥቅም ላይ ማዋሉ ተገልጿል።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ዘሐራ መሐመድ ፕሮጀክቱ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረው የነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት በማቃለሉ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለአጭር ጊዜ አገልግሎት ሰጥቶ እንዳይቋረጥ  የጉባ ወረዳ አስተዳደር በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

ወይዘሮ መኪያ መሐመድ በበኩላቸው የከተማዋ ውሃ ችግር በተለይም በእናቶችና ሴቶች ኑሮና ትምህርት ላይ ጫና ሲያሳድር መቆየቱን  ያስታውሳሉ ፡፡

ከዚህ ቀደም በአካባቢው የነበረው የመጠጥ ውሃ ከወንዝ ለመቅዳት የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ ለማድረግ ይገደዱ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

የጉባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብደላ ኢብራሂም በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ዘላቂ  አገልግሎት እንዲሰጥ የወረዳው አስተዳደር ትኩረት መስጠቱን ይናገራሉ።

በዚህም አሁን በጄኔሬተር የሚደረገውን የውሃ ግፊት በኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ለመተካት ከሚመለከተው አካል ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከውሃ የሚገኘውን ገቢ መልሶ ለመጠቀም  ጽህፈት ቤት የማደራጀትና የሰው ኃይል ማሟላት ተግባራት እንደሚከናወኑም  ገልጸዋል፡፡

በተለይም የአካባቢ ጥበቃ ሥራውን በዘላቂነት በማካሄድ አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ጥረት እንደሚደረግ ዋና አስተዳሪው አመልክተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በክልሉ ኅብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት በበጀት እጥረት ምላሽ ሳያገኝ እንደሚቀር ገልጸዋል።

ለዚህም ረጅም ጊዜን የፈጀው የከተማዋን ሕዝብ የውሃ ጥያቄ ዋነኛ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የማንኩሽ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የነዋሪዎችን የመጠጥ ውሃ ፍላጎት እንደሚያሟላ ተናግረዋል፡፡

ኅብረተሰቡ የአካባቢውን ሠላም እንዲጠብቅና የውሃ ተቋሙን በእንክብካቤ እንዲጠቀም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡

ግንባታውን ላከናወነው የአማራ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም