የለሙ ተፋሰሶችን ከሰውና እንስሳት ንክኪ እየጠበቅን ነው-የፎገራ ወረዳ አርሶ አደሮች

61

ጎንደር ጥር 20/2011 በማዕከላዊ ጎንደር የፎገራ ወረዳ አርሶ አደሮች የተፋሰስ ልማት የተካሄደባቸውን አካባቢዎች ንክኪ የሚጠብቁበት መተዳደሪያ ደንብ ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን ገለጹ።

በለሙ የተፋሰስ አካባቢዎችን ለእንሰሳት እርባታ፣ ማድለብና ንብ ማነብ ሥራዎች በማዋል ገቢያቸውን እያሳደጉበት መሆኑንም  ተናግረዋል።

ከአርሶ አደሮቹ መካከል ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በወረዳው የተፋሰስ ልማት የተካሄደባቸውን አካባቢዎች ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ የሚጠብቁበት ደንብ አውጥተው እየተገበሩ ናቸው።

ከአርሶ አደሮቹ የታጋ ቀበሌው አርሶአደር ገብሩ ተሰማ በቀበሌያቸው ያገገሙ ተፋሰሶች የጥበቃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ደንቡ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

"ደንቡ ካካተታቸው ጉዳዮች መካከል በለሙ ተፋሰሶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ግለሰቦች ከ500 እስከ 700 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲከፍሉ የሚለው ተጠቃሽ ነው " ብለዋል።

"በተስማማንበት ሕገ-ደንብ መሠረት የለሙ ተፋሰሶች ከንክኪ ተከልለው እየተጠበቁ ነው።የለሙ አካባቢዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ አርሶ አደር እንዲቀጣ እያደረግን ነው" ያሉት ደግሞ የጀጀህ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሲሳይ ማንደፍሮ ናቸው፡፡

የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አቤ አስፋው "በወረዳው ባለፉት ዓመታት በህዝብ ተሳትፎ ለለሙ 47 ተፋሰሶች አርሶ አደሩ ጥበቃ እያደረገላቸው ነው" ብለዋል ።

አርሶ አደሩ የተፋሰስ ጥበቃ ኮሚቴና መተዳደሪያ ደንብ በማውጣት ተፋሰሶችን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ እየጠበቀ መሆኑንም መስክረዋል ።

በሦስት ተፋሰሶች ላይ ከብቶችን በማሰማራት ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ሰባት ግለሰቦች በየቀበሌዎቹ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ቀርበው እያንዳንዳቸው በ500 ብር እንዲቀጡ መደረጉን አስታውቀዋል።

በወረዳው በዘንድሮ የበጋ ወራት"ጤናማ አፈር ለጤናማ ህይወት!" በሚል መሪ ቃል ለአንድ ወር የሚቆይ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በልማቱ ከ37ሺህ በላይ ህዝብ ይሳተፍበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም