ባለስልጣኑ ለ5 የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃድ ሰጠ

114

አዲስ አበባ ጥር 20/2011 የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ባለፉት ስድስት ወራት ለአምስት በሳተላይት የሚያሰራጩ የንግድ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ መስጠቱን ገለጸ።

ባለስልጣኑ ይህን የገለጸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸሙን ሲያቀርብ ሲሆን ቋሚ ኮሚቴው ፈቃድ መስጠት ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነት ላይም በትኩረት መስራት አለብህ ተብሏል።

በስድስት ወራት በሳተላይት አማካኝነት የሚሰራጭ የንግድ ቴሌቪዥን ብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ ለጠየቁ አምስት አመልካቾች ፈቃድ  መስጠቱን ገልጿል።

ኦ ኤም ኤን፣ ኦ ቢ ኤስ፣ ሃይ አስ፣ ባላገሩ እና ኦያያ መልቲ ሚዲያዎች ፈቃድ የተሰጣቸው የንግድ ቴሌቪዥን ብሮድካስት አገልግሎቶች ናቸው።

ባለስልጣኑ ለኢሳትና አሃዱ ቴሌቪዥን መስፈርቱን ሲያሟሉ ፈቃድ ለመስጠት መዘጋጀቱንም ገልጿል።

ፈቃድ ከመስጠት ባሻገር የሚተላለፉ መረጃዎች ተአማኒነት፣ ሚዛናዊነትና የህብረተሰቡን ሰላም የማያደፈርሱ መሆንና አለመሆናቸውን እንዴት ትቆጣጠራለህ ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጠይቀዋል።

መገናኛ ብዙሃን የአገር አንድነትና ብዝሃነትን በሚያከብር መልኩ መረጃዎችን ማሰራጨት እንዳለባቸው በብሮድካስት አዋጁ ቢቀመጥም በተወሰኑት ላይ ከዚህ በተቃራው ሲተገበር ይስተዋላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ተስፋዬ "በኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች የሚያሰራጩት መረጃዎች በሙሉ ታአማኒ፣ ሚዛናዊና ወገናዊ ያልሆኑ ናቸው ማለት አይቻልም" ሲሉ ተናግረዋል።

ሊያሻሽሉ የሚገባቸውንና ተጨማሪ መስራት ያለባቸውን በየዕለቱ ከሚያሰራጩት መረጃ በመነሳት ተቋሙ ግብረ-መልስ እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

"በብሮድካስተሮች ስርጭት ውስጥ የሚስተዋሉ ህጸጾች ዘንድሮም አሉ የሚቀጥለው ዓመትም መኖራቸው አይቀርም" በማለት የብሮድካስት ኢንዱስትሪው አለማደጉ ለችግሩ መቀጠል ምክንያት መሆኑን አቅርበዋል።

አቅም ባለመኖሩም ስነ-ምግባር የጎደለው ስራ ሁሌም እንደሚኖር በማንሳት የአቅም ግንባታ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ህገ-መንግስቱን የጣሰ ተግባር ከሰሩ በአዋጁ መሰረት እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት።

ዋና ዳይሬክተሩ በአብዛኞቹ ብሮድካስተሮች ሚዛናዊና መፍትሔ አዘል ዘገባ ማቅረብ ልምድ እየሆነ መምጣቱን ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል።

የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን የህዝብ አንድነት የሚያደፈርስ ዘገባ የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙሃን ላይ ተቋሙ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

ባለስልጣኑ ፈቃድ ለሚሰጣቸው ተቋማት ጥሩ የሚሰሩትን የሚያበረታታ ጥፋተኞችን ተጠያቂ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋት ይኖርበታል ብለዋል ሰብሳቢዋ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የዲጂታል ቴሌቪዥን ቴክኖሎጂ ሽግግር ወደ ትግበራ መግባት ካለበት ጊዜ በመዘግየቱ በትኩረት መስራት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

በኢትዮጵያ በሳተላይት የሚያሰራጩ የንግድ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥር 16 መድረሱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም