የከተሞች የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ስራ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እየተከናወነ አይደለም

111

አዲስ አበባ ጥር 20/2011 የከተሞች የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ስራ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እየተከናወነ አለመሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።

የፌዴራል የከተማ መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ ኤጀንሲ በበኩሉ ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን የፖለቲካው ሁኔታና የክልል አመራሮች ድጋፍ ማነስ ምክንያት ነው ብሏል።

በምክር ቤቱ የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኤጀንሲውን የስድስት ወር የስራ አፈጻጻም ዛሬ ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ጋዕሚ በዚሁ ወቅት እንዳሉት " የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና ማረጋገጥ ስራ ኤጀንሲው በተደጋጋሚ ውጤት ያላስመዘገበበት ተግባር ነው"።

ኤጄንሲው ኮሚቴው በተደጋጋሚ የሚሰጠውን ግብረ መልስ ተቀብሎ ከማስተካካል አንጻር መዘግየት እንደሚታይበትም ጠቁመዋል።

በዚህም ምክንያት በመሬት ጉዳይ በአገሪቷ የሚስተዋለውን ሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግር መፍታት እንዳልተቻለም ቋሚ ኮሚቴው አስታውቋል ።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና በበጀት ዓመቱ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካትም ኤጀንሲው አቅሙን አሟጦ እንዲጠቀም ምክር ቤቱ አሳስቧል።

ባለፉት ስድስት ወራት ተቋሙ በበርካታ የድጋፍና ክትትል ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም ቢያከናውንም በቁልፍ ስራዎቹ የከተማ መሬት ምዝገባና ይዞታ ማረጋገጥ ተግባር ውስንነቶች በተደጋጋሚ ተስተውሏል።

ኤጀንሲው ባለፉት ስድስት ወራት 81ሺህ 550 የመሬት ይዞታዎችን የማረጋገጥ ስራን ለማከናወን አቅዶ 45 ሺህ የሚሆነውን ብቻ  ማከናወን መቻሉ ተገልጿል።

በተጨማሪም በክልል ከተሞች 74 ሺህ 280 የመሬት ይዞታዎችን ለመመዝገብ አቅዶ  46 በመቶውን ብቻ ማሳካት እንደቻለ ነው የተገለጸው።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ከበደ እንዳሉት "የተቋሙ ተግባር በራሱ ብቻ የሚተገበር ባለመሆኑና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ከፍተኛ በመሆኑ የተያዘውን ዕቅድ በአግባቡ ለመተግበር አልተቻለም"።

በተለይ ክልሎች ተቋማትን አደራጅተው ወደ ስራ ማስገባት ላይ የመጓተትና የቁርጠኝነት መጓደል ማሳየታቸው ለስራቸው እንቅፋት እንደሆነ  ተናግረዋል።

በተጨማሪ የበጀትና የግብዓት ዕጥረት፣ ከፍተኛ የሰው  ሃይል ፍልሰት፣ አገራዊ ሶፍትዌር በተያዘለት የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቅና ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ወቅቱንና ጥራቱን የጠበቀ ሪፖርትና  መረጃዎችን ተደራሽ ያለማድረግ የተቋሙ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ጥቂት የክልል ከተሞች የስራ ሃላፊዎች ለተያዘው አገራዊ ተግባር የሚያደርጉትን ድጋፍ  እንደ ተሞክሮ በማስፋትም ችግሩን ለመፍታት ይሰራል ብለዋል።

የፖለቲካ አመራሩ በጉዳዩ ላይ በቂ አረዳድና ቁርጠኝነት እንዲኖረውም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላልን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም