በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ የማድረጉ ተግባር ሊጠናከር ይገባል ተባለ

91

አዲስ አበባ ጥር 20/2011 በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ አድርጎ ለማደራጀት የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ተባለ።

የኢትዮጵያ የመብት ድርጅቶች ህብረት፤ መቀመጫውን ጄኔቫ-ስዊዘርላንድ ካደረገው 'ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ' ከተሰኘ ተቋም ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ የመከረ ውይይት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል።

ህብረቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፣ ቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረንስ ፎር ዲሞክራሲ፣ አድቮኬትስ ኢትዮጵያ፣ ዴቨሎፕመንታል ጀስቲስ ናሽናል አሶሲየሽንና ሳራ የሴቶች ፍትህ ማህበር የተሰኙ ማህበራትን በስሩ ይዟል።

የህብረቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ እንዳሉት፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደስልጣን መምጣት በኋላ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እየተሻሻለ ቢሆንም አሁንም የዜጎችን መብቶች ለማስከበር ብዙ መስራት ይጠበቃል። 

መንግስት የሲቪክ ማህበራትን የተመለከተው አዋጅን ጨምሮ ምርጫ ቦርድ፣ የጸረ ሽብር ህጉን ለማሻሻል እንቅስቃሴ መጀመሩ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ትልቅ በር ይከፍታል ሲሉም ነው አቶ መሱድ የገለፁት።

"የፍትህ አካላትን ለማሻሻል የከፍተኛ አመራሮች ለውጥ ቢደረግም ወደ ታች ሲወርድ ግን ገና ለውጥ እንዳላመጣ አረጋገጠናል" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ስለሰብዓዊ መብት መከራከር ቀርቶ ስሙን ማንሳት የማይቻልበትን ጊዜ አሳልፈናል ያሉት አቶ መሱድ፤ አሁን ያለው ተስፋ ቀጣይነት እንዲኖረው ነጻና ገለልተኛ ተቋማዊ አደረጃጀትን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ሊጠናከር ይገባል ሲሉም አመልክተዋል።

"እና እንደ ሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ማህበርነታችን መታወቂያና የደረት ባጅ በመያዝ የታሰሩ ዜጎችን ሰብዓዊ መብት አያያዝ መመልከት ሲገባን ፈቃድ አልተሰጠም፣ ከበላይ አካል ደብዳቤ አምጡ፤ ቀጠሮ አስይዙ" እየተባሉ እንደሚመለሱም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለዜጎች ሰብዓዊ መብት ጥብቅና መቆሙን ለማረጋገጥ በማንኛውም ጊዜ ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ እንጂ ቀጠሮ በማስያዝ አይደለም በማለትም አቶ መሱድ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ያለው የዜጎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል ከመንግስት ጋር በቅርበት በመስራት የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል። 

መቀመጫውን ጄኔቫ-ስዊዘርላንድ ያደረገው ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ መፍቀዱን አድንቀዋል።

ይሁን እንጂ አሁን የተፈጠረው የፖለቲካ ምህዳር ሰፍቶ እንዲቆይ፤ ፍትህ እንዲሰፍንና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቆም የተጀመረው ተቋማዊ አደረጃጀት መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም