አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በተከሰሱበት የኢምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ላይ የክስ መቃወሚያቸውን አቀረቡ

1128

አዲሰ አበባ ጥር 20/2011 የአክሰስ ሪል ስቴት ባለቤት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በተከሰሱበት የኢምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ላይ የክስ መቃወሚያቸውን አቀረቡ።

ዐቃቤ ሕግ የአክሰስ ሪል ስቴት መስራች በሆኑት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ በመተላለፍ በሚል ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም ክስ መስርቶባቸዋል።

በዛሬው እለትም አቶ ኤርሚያስ  ከኢምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ጋር በተያያዘ ዐቃቤ ሕግ በመሰረተባቸው ክስ ላይ ለፍርድ ቤቱ 15ኛ ወንጀል ችሎት መቃወሚያቸውን በጠበቃቸው በኩል በጽሑፍ አቅርበዋል።

በዚህ መሰረትም አቶ ኤርሚያስ የተከሰሱበት የክስ ተሳትፎ ምን እንደሆነ በግልጽ አለመቀመጡን ፣ በክሱ ላይ የተጠቀሰው አንቀጽ 33 በልዩ ወንጀል የተካፈሉበትና የፈፀሙት ወንጀል በግልጽ እንዳልተቀመጠ በመቃወሚያ ጽሑፋቸው ላይ ተቀምጧል።

በተጨማሪም ”ምን ማድረግ ሲገባኝ ያላደረግኩት፤ ማድረግ ሳይገባኝ ያደረኩት ነገር አለ? ይህንን ክሱ አይገልጽም” ሲሉም በመቃወሚያቸው አንስተዋል።

በሆቴሉ ሽያጭ ላይ የዐቃቤ ሕግ  የዋጋ መተመኛ ስታንደርድ ምንድን ነው? አገራችን እየተከተለች ያለችው ነጻ የገበያ ውድድር እንጂ የእዝ ኢኮኖሚ  የገበያ ዋጋ አይደለም የሚልም ካነሱዋቸው የክስ መቃወሚያ ሐሳቦች መካከል ናቸው።

በዚሁ የክስ መዝገብ ቁጥር 229498 ፤ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኝው፣ ኮሎኔል በርሃ ወልደሚካኤል/ያልተያዙ/፣ ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርኤል፣ ብርጋዴል ጄነራል በርኸ በየነ፣ ሌተናል ኮሌኔል ስለሺ ቤዛ /ያልተያዙ/፣ ወይዘሮ ሲሳይ ገብረ መስቀል/ያልተያዙ/ ፣አቶ ዓለም ፍጹም፣ሌተናል ኮሎኔል ግርማ ዳምጤ፣ ሻምበል አግዘው አልታዬና አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ይገኙበታል።

ፍርድ ቤቱ የአቶ ኤርሚያስ አመልጋን ጨምሮ በሌሎች 11 ተከሳሾች ላይ የዐቃቤ ሕግን ምላሽ ለመስማት ለጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።