አዲስ ለተሾሙ አምባሳደር ባለቤቶች የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲን በሚመለከት ስልጠና ይሰጣል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

103

አዲስ አበባ ጥር 20/2011 አዲስ ለተሾሙ አምባሳደር ባለቤቶች የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲን በሚመለከት ስልጠና እንደሚሰጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ኢንስትቲዩት አዲስ ለተሾሙ አምባሳደሮች የሚሰጠውን ስልጠና ዛሬ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

አምባሳደሮቹ በሚሰማሩበት አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሚሲዎኖችን ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፉ በማድረግ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ መሰራት እንዳለባቸውም ዶክተር ወርቅነህ በዚሁ ጊዜ ገልፀዋል።

የዲፕሎማሲ ስራ ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን የጠቆሙት ሚንስትሩ፤ አምባሳደሮቹ ከመቶ ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች ተወካይ መሆናቸውን ተገንዝበው ስራቸውን በሃላፊነት እንዲከውኑ አሳስበዋል።

አምባሳደሮቹ በየሚሰማሩበት አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም የበኩላቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በዲፕሎማሲ ስራ ላይ ከአምባሳደሮች በተጨማሪ የአምባሳደሮቹ ባለቤቶች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የጠቆሙት ዶክተር ወርቅነህ፤ ይህን ከግንዛቤ በማስገባት አዲስ ለተሾሙት የአምባሳደር ባለቤቶች የአንድ ቀን ሰልጠና ይሰጣል ብለዋል።

ዛሬ የተጀመረው ስልጠና ለቀጣይ አስር ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ሃያ አምባሳደሮችና ሁለት የሚሲዎን ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ተሳታፊዎች ናቸው።

የአምባሳደር ባለቤቶች ስልጠናም በመርሃ ግበሩ ማጠቃለያ ላይ እንደሚሰጥ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም