ቮልስዋገን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነት ፈረመ

162

አዲስ አበባ ጥር 20/2011 ግዙፉ መኪና አምራች ኩባንያ ቮልስዋገን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ፈረመ። 

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አበባ አበባየሁ እና ከሰሃራ በታች የኩባንያው የአፍሪካ ቀጣና ሥራ አስፈጻሚ ቶማስ ሻፈር ተፈራርመዋል።

በስምምነቱ ላይ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዋልተር ስታይንማየርና የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ተገኝተዋል።

ኩባንያው ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያን የማስፋፊያ ማዕከሉ አድርጎ መርጧታል።   

ኢትዮጵያም ከጋና እና ናይጄሪያ ቀጥሎ ስምምነቱን የፈረመች ሦስተኛዋ አገር ሆናለች።  

ኩባንያው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመስራት መስማማቱ በቀጥታ የእሴት ሰንሰለት የተቀናጀ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ክላስተር ለመፍጠር ወሳኝ ምዕራፍ ይከፍታል ነው የተባለው።

ኮሚሽነር አበበ በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት መንግሥት አገሪቷን ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ነው።     

''በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው መስክ ልዩ ክላስተር እንዲመሰረት መንግሥት ያለሰለሰ ጥረት ያደርጋል'' ያሉት ኮሚሽነሩ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ቮልስዋገንን ጨምሮ ፍላጎት ካላቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመስራት 'ዝግጁ ነው' ብለዋል።

የኩባንያው የአፍሪካ ቀጣና ሥራ አስፈጻሚ ቶማስ ሻፈር በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ለአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው እድገት ትኩረት መስጠቱ 'የሚደነቅ ነው' ሲሉ ተናግረዋል።   

በኢትዮጵያ እንድንሰራ ለተደረገልን ድጋፍ 'ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ' ያሉት ሥራ አስፈጻሚው ስምምነቱ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት ለምንሰራው ስራ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም