ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጀርመን ለኢትዮጵያ እያደረገች ስላለው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገለፁ

191

አዲስ አበባ ጥር 20/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጀርመን ለኢትዮጵያ እያደረገች ስላለው የቆየና ቀጣይነት ያለው የቴክኒክና የሞያ ድጋፍ አድናቆታቸውን ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ካሉት የጀርመን ፌዴራል ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ስታይን ማየር ጋር ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀርመን መንግስት ለኢትዮጵያ እያደረገ ያላለውን ቴክኒካዊና ሞያዊ ድጋፍ አድንቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ለተመዘገበው ስኬት ግለሰቦች፣ ሀሳቦች እና ተቋማት ዋና ዋና መሰረቶች መሆናቸውንም ለጀርመኑ ፕሬዚዳንት አብራርተውላቸዋል።

ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ስታይንማየር በበኩላቸው የኢትዮ-ጀርመን ግንኙነት ለውጥን ወደ መደገፍ ትብብር ከፍ ማለቱን ገልፀዋል።

በቀጣይ እርሳቸውና መንግስታቸው ይህንኑ የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩም ለዶክተር ዓብይ አረጋግጠውላቸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ የአራት ቀናት የስራ ጉብኝት ለማድረግ ትናነት ማምሻውን ነው አዲስ አበባ የገቡት።

የኢትዮጵያና ጀርመን የልማት ትብብር ከ50 ዓመታት በላይ የዘለቀ ታሪክ ያለው ሲሆን ጀርመን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት፣ ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና እንዲሁም ለግብርና ዘርፍ ልማት ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች።

ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ከሚያደርጉት ውይይት በተጨማሪ በጀርመን የልማት ትብብር የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያና ጀርመን በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ  በተደጋጋሚ ጉብኝቶችን በማድረግ ላይ ሲሆኑ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ሁለት የጀርመን ሚኒስትሮች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዎልተር ስታይነር እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር 2017 ወደ ፕሬዝዳንትነት ከመምጣታቸው በፊት ለሰባት ዓመታት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፤ በአውሮፓዊያን 2014 ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም ጀርመንን መጎብኘታቸውም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም