የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ የክልሎችን ህገ-መንግስታዊ ስልጣን ይጋፋል---የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ

189

መቀሌ ጥር 20/2011 የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ህገ-መንግስቱ ለክልሎች የሰጠውን ስልጣን የሚጋፋ መሆኑን የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 9ና 13 አንቀጽ መሰረት ህገ መንግስቱ እንዳይጣስ የማክበርና የማስከበር ግዴታ ለክልሎችና ለፌደራል ህግ አውጪዎችና አስፈጻሚዎች የማክበር ግዴታና ህገ-መንግስታዊ ስልጣን አላቸው፡፡

የክልሉ ምክር ቤትም በህገ-መንግስቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ ተፈጻሚ እንዳይሆን በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን አስረድተዋል።

በርቅቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ የፀደቀው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን መቋቋሚያ አዋጅ የህገ-መንግስት ትርጉም የሚያስነሳ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት ሰሞኑን የወሰደው አቋም የህገ-መንግስቱን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤቶች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን መብት ለማስከበር ካለው ፍላጎት የመነጨ መሆኑንም የቢሮ ኃላፊው አቶ አማኑኤል አሰፋ አስረድተዋል።

 “በህገ-መንግስቱ መሰረት ፌዴራል መንግስትን ያቋቋሙት ክልሎች እንጂ እሱ ክልሎች አላቋቋማቸውም” ብለዋል፡፡

ህገ-መንግስቱን የመጠበቅና የማስጠበቅ በቅድሚያ የክልሎችና ክልሎችን ያቋቋሙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን አስረድተዋል።

“በመሆኑም ሚኒስትሮች ምክር ቤትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሌሎች አዋጆች እንጂ የህገ-መንግስት ጉዳዮችን የሚመለከቱ አዋጆችን የማውጣት ስልጣንና ሃላፊነት የላቸውም” ብለዋል።

 “በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 62 መሰረት በክልሎች መካከል ለሚነሱ የወሰን ጉዳዩች በቅድሚያ መፍታት የሚገባቸው የጉዳዩ ባለቤቶች ናቸው” ብለዋል፡፡

“ክልሎች መፍታት ካልቻሉ ደግሞ  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚያቋቁማቸው ኮሚቴዎችና የህገ-መንግስቱን ጉዳይ በሚያየው አካል መታየት እንዳለበት በግልፅ ተቀምጦ እያለ ከዚህ ውጭ መሄድ የህገ-መንግስትን ጥሰት ያሳያል” ብለዋል።

በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 51 ለፌዴራል መንግስት ከተሰጠው ስልጣን ውጭ የክልሎች መሆኑን በግልፅ ያሳያል ብለዋል፡፡

“አንቀፅ 52 ለክልሎች የሰተጠው ስልጣንና ተግባር እንዲሁም በአንቀፅ 62 ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠው መሆኑን ህገ-መንግስቱ ይደነግጋል” ብለዋል፡፡

አንቀፅ 83 ህገ-መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን ያለው የማን መሆኑን የሚያስረዱ አንቀፆች በዚህ አዋጅ መጣሳቸውን የክልሉ ምክር ቤት በመጥቀስ አቋም እንደወሰደ አስረድተዋል።

“በህገ-መንግስቱ አንቀፅ ሁለት ክልሎች የአገሪቱ የወሰን ባለቤቶች ናቸው የሚለውና የኮሚሽኑ ስያሜ ከህግ አንፃር የተለያየ ትርጉም አላቸው” ብለዋል፡፡

“የአስተዳደር ወሰን” የሚለው ሀረግ አሃዳዊ/የግዛት አንድነት/ ከማራመድ አንፃር የሚያያዝና በህገ-መንግስቱ የማይገኝ ስያሜ መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ  ምክር ቤት ጉዳዩን በጥልቀት ከመረመረ በኋላ አዋጁ የአገሪቱን ህገ-መንግስት የሚጥስና የስልጣን ባለቤቶቹን ህገ-መንግስታዊ መብት የሚጋፋ መሆኑን በመጥቀስ ተቃውመውታል ብለዋል፡፡

እንዲሁም የወሰን ጉዳዮች የሚያዩና በህገ-መንግስቱ የተቀመጡ አካላት መብት የሚጋፋ በመሆኑ ተግባራዊ እንዳይሆን የውሳኔ ሃሳብ ማስተላለፉን አስረድተዋል።

የክልሉ ምክር ቤት በ5ኛው ዘመን 14ኛው መደበኛው ጉባኤው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ በቅርቡ የፀደቀው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ተግባራዊ እንዳይደረግ በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም