በዛፍ እስከ 100 ኪሎ ግራም ቴምር የሚሰጡ ዝርያዎች በአፋር ተገኙ

1623

ሰመራ  ጥር 20/2011  በአፋር ክልል ለዘመናት በዝቅተኛ ደረጃ  የሚመረተውን ቴምር በዛፍ  እስከ 100 ኪሎ ግራም የሚሰጡ ሦስት ዝርያዎች ማግኘቱን የአፋር ክልል አርብቶ አደር ምርምር አንስቲትዩት አስታወቀ።

በክልሉ   ከቴምር ዛፎች የሚሰበሰበው በዛፍ ከ25 ኪሎ ግራም አልፎ እንደማያውቅም አምራቾቹና ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

በማዕከሉ የሰብል ምርምር ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አህመድ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስረዱት ዝርያዎቹ የተገኙት በሦስት ወረዳዎች በከፊል አርብቶ አደሮች ማሳ በተደረገ ምርምር ነው።

ዝርያዎቹ በአካባቢያዎቹ ካሉት አገር በቀል የቴምር ዛፎች በአማካይ ከሚሰጡት እስከ አራት እጥፍ ብልጫ ምርት እንደሚሰጡ አስረድተዋል።

ዝርያዎቹ ቀድሞ በሰባት ዓመታት  ውስጥ ይደርስ የነበረውን ምርት  ወደ ሦስት ዓመታት ለማውረድ ያስችላሉ ብለዋል።

በአይሳኢታ፣በአፋምቦና በአሚባራ ወረዳዎች ከተገኙት መካከል በአንድ ዛፍ 100 ኪሎ ግራም  ምርት የሚሰጠው ”መጁኢን” የተባለው ዝርያ ይገኝበታል።

በዛፍ 80 ኪሎ ግራም ምርት የሚሰጡ ደግሞ ”ካህላስ”ና ”በርሄ” የተባሉ ሁለት ዝርያዎችም ሌሎቹ የምርምሩ ውጤቶች መሆናቸውን አቶ መሐመድ ተናግረዋል።

የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ተቋቁመው  ባለፉት ስምንት ዓመታት ከውጭ በገቡ 14 ዓይነት ዝርያዎች በማዕከሉና በሙከራ ጣቢያዎች በተደረገው በማዳቀል መገኘታቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ከጀርመን የቴክኒክ ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ)በተደረገ የድጋፍ የተገኙትን ዝርያዎች በዱብቲና ገዋኔ ወረዳዎች ለማስፋፋት ከ3ሺህ ችግኞች መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።

ዝርያዎቹ  ከሰድስት ወራት በኋላ ለወረዳዎቹ  ከፊል አርብቶ አደሮች አንደሚሰራጩም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። 

በአፋምቦ ወረዳ የሁመዶይታ ቀበሌ ከፊል አርብቶ አደር አቶ ከቢር ጂላኒ ቴምር የሚያስገኘውን ጥቅም በመረዳት በአካባቢያቸው ከተቋቋመው የችግኝ ጣቢያ ዝርያውን በመውሰድ በማልማት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በዚሁ ቀበሌ የሊዕመሌ የቴምር አምራቾች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ሐቢብ ሰዒድ ከማዕከሉ የተሰጧቸውን 310 የቴምር ችግኞች በማልማትና በመንከባከብ እሳቸውና የማህበሩ አባላት ተጠቃሚ እየሆንን ነው ብለዋል።

የማህበሩ አባላት ከምርቱ ያገኙትን ከ100 ሺህ ብር በላይ በመቆጠብ ሥራቸውን ለማስፋፋት ማቀዳቸውን ተናግረዋል። 

የአፋር ክልል ባለው የከፊል በረሃነትና የበረሃነት የአየር ጸባይ ባህርይ ለቴምር ልማት ምቹነት አለው።