የተፋሰስ ልማት ሥራ ምርታማ አድርጎናል.. የስልጤ ዞን አርሶ አደሮች

174

ሀዋሳ ጥር 20/ 2011ዓ.ም ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች  ምርታማነታቸውን እንዳሳደገው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የስልጤ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።

በክልሉ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወነ የተፋሰስ ልማት  ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የተጎዳ መሬት እንዲያገግም መደረጉን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሁልባረግና አሊቾ ውሪሮ ወረዳ አርሶ አደሮች እንዳሉት የተፈጥሮ ሀብቱ መጎዳት ከማሳቸው የሚያገኙት የግብርና ምርት ከመቀነሱ ባለፈ በተደጋጋሚ በጎርፍ ሲጠቁ ቆይተዋል።

በሁልባረግ ወረዳ የሀምበርቾ አጫሞ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አክመል ሼህ መሀመድ እንዳሉት የሚኖሩበት ተራራማ አካባቢ በመጎዳቱ ማሳቸው የሚሰጠው ምርት መጠን አነስተኛ ነበር።

ክረምት በመጣ ቁጥር ከተራራው የሚወርደው ጎርፍ ከሚያደርሰው ጉዳት ባለፈ የማሳቸውን ለም አፈር ጠርጎ በመውሰድ ለጉዳት ዷርጓቸው እንደነበር ገልጸዋል።

"በአካባቢያቸው የተፋሰስ ሥራ መስራት ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ መሬቱ ቀስበቀስ እያገገመና እየተለወጠ መጥቷል፤ በእዚህም የሰብል ምርታችን ከመጨመሩ ባለፈ ለእንስሳት መኖ ሳር ማግኘት ችለናል" ብለዋል።

የአሊቾ ውሪሮ ወረዳ ኤዶ ቁጥር ሁለት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አስራር ሀሊድ በበኩላቸው እንዳሉት ማሳቸው በውሀ ታጥቦ አፈሩ በመወሰዱ ምክንያት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምንም ምርት የማይሰጥ ደረቀ መሬት ሆኖ ነበር።

ቀደም ሲል ከአስር ኩንታል ምርት በላይ አግኝተው እንደማያቁ የጠቆሙት አርሶ አደሩ ለተዳፋታማው መሬታቸው ጠረጴዛማ እርከን በመስራታቸው መሬቱ ማገገሙና በአሁኑ ወቅት እስከ 50 ኩንታል ምረት ማግኘት እንደቻሉ ጠቁመዋል።

የአሊቾ ውሪሮ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ተከተል አበበ እንዳሉት በወረዳው በተራራማ አካባቢዎች ላይ ጎርፍ  አፈሩን አጥቦ ከመውሰድ ባለፈ መሬቱን አሲዳማ አድርጎት እንደነበረ ተናግረዋል።

ይህን ችግር ለማስወገድ ባለፈው ዓመት 1 ሺህ ኩንታል ኖራ በመጠቀም መሬቱን ከአሲዳማነት ማስቀረት እንደተቻሉ ገልጸዋል።

በተፋሰስ ልማቱ የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል በሁልባረግ ወረዳ የሀምበርቾ አጫሞ ቀበሌ የሚኖሩት ወይዘሮ ሙልፊት ዋልቀሮ እንዳሉት በዐረብ ሀገር ብዙ ችግር አይተው እንደመጡና አሁን በአካባቢው በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል አርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ መና በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወነ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንዲለማ ተደርጓል።

የተፈሰስ ልማት ስራው ሲጀመር 11 በመቶ ብቻ የነበረው የክልሉ የደን ሽፋን በአሁኑ ወቅት ወደ 22 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ ማለቱንም ነው ያስረዱት።

በተፋሰስ የለሙ አካባቢዎች ላይ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንም አቶ መለሰ ጠቁመዋል።

በየጊዜው የተከናወኑትን ሥራዎች የሚገመግም ጥናት መካሄዱን ገልጸው በዚህም በአፈር ለምነት፣ በደን ሽፋን፣ በውሃ መጠን መጨመርና በእንስሳት መኖ አቅርቦት ላይ ለውጦች መታየታቸውን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በመስኖ ይለማ የነበረው የመሬት መጠን ከ100 ሺህ ያነሰ እንደነበር ገልጸው በአሁኑ ወቅት ይህ ቁጥር ወደ 500 ሺህ ሄክታር ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በክልሉ በአጠቃላይ የተፋሰስ ልማት ሥራው ከተጀመረ ወዲህ የግብርና ምርትና ምርታማነት መጠን እየጨመረ መምጣቱንም አቶ መለሰ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም