በአላማጣ ከተማ በ125 ሚሊዮን ብር ወጪ ለሚገነባው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

61

ማይጨው  ጥር 20/2011 በትግራይ ደቡባዊ ዞን አላማጣ ከተማ በ125 ሚሊዮን ብር ወጪ ለሚገነባው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የመሰረት ድንጋዩ ትናንት በተቀመጠበት ወቅት እንደተገለጸው ፋብሪካው የሚገነባው ራያ አግሮ ኢንዱስትሪ ኩባንያ በተባለ የግል ተቋም ነው።

የኩባንያው ቦርድ አባላት ለፋብሪካው ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ካስቀመጡ በኋላ በኩባንያው ዓላማና የልማት ዕቅድ ላይ ከአካባቢው ነዋሪዎችና የመስተዳድር አካላት ጋር ተወያይተዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የኩባንያው ቦርድ ሰብሰቢ ዶክተር ሞላ መንግስቴ እንዳሉት፣ የፋብሪካው ግንባታ የሚካሄደው የከተማው አስተዳደር ለኩባንያው በማበረታቻነት በሰጠው 20 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው፡፡

የፋብሪካው ግንባታ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም አመልክተዋል።

ኩባንያው በአላማጣ ከተማ ለሚገነባው የወተት ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግንባታ የሚውለውን ገንዘብ የሚሸፈነው ከባንክ ብድር፣ ከአክሲዮን ሽያጭና ከኩባንያው ባለ ድርሻ አባላት በማሰባሰብ መሆኑንም አስረድተዋል።

ፋብሪካው ከቅባት ነፃ የሆኑ የፈሳሽና ዱቄት ወተት ምርቶችን እሴት በመጨመርና በተለያየ መልክ በማቅረብ ወደ ገበያ የማቅረብ ተልእኮ አለው።

"ከዚህ በተጨማ ለቼዝና ቸኮሌት ምግቦች መስሪያ የሚውሉ የወተት ተዋፅኦ ምርቶችን በማምረትና በማሸግ ወደ ገበያ ያቀርባል" ብለዋል ፡፡

ዶክተር ሞላ እንዳሉት ፋብሪካው በአካባቢው በወተት ላሞች እርባታ የተሰማሩ አርሶአደሮች የወተት ምርትን በመረከብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡

ኩባንያው ከወተት ምርት ማቀናባበር ጋር ተያይዞ አዳዲስ የሥራ አማራጮችን በማምጣትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎን በማስተዋወቅ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ማለሙንም ተናግረዋል፡፡

እነደ ዶክተር ሞላ ገለጻ፣ የወተት ማቀናባበሪያ ፋብሪካው በአካባቢው ለሚኖሩ 220 ያህል ሰዎች የሥራ እድል ተጠቃሚ ያደርጋል።

የኩባንያው የቦርድ አባል ዶክተር ምትኩ ኃይለ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ፋብሪካው ዘርፉን ከማሳደግ ባለፈ የአካባቢው አርሶ አደር ከእንስሳት ሃብቱ የሚያገኘው ጥቅም ለማሳደግ ይሰራል።

ኩባንያው የፋብሪካው ግንባታ ካጠናቀቀ በኋላም ተጨማሪ 300 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቁ ሌሎች የግብርና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በአካባቢው ለማከናወን ማቀዱንም ጠቁመዋል።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም የወተት ላሞች እርባታ፣ የከብቶች ማድለቢያ፣ የእንስሳት መኖ ልማትና የመኖ ማቀነባበሪያ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበት ነው የገለጹት።

ፕሮጀክቶቹ ተገንብተው ሲጠናቀቁም ለተጨማሪ 900 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

በውይይቱ ከተሳተፉት አርሶአደሮች መካከል በራያ አላማጣ ወረዳ የሰላም ብቃልሲ ነዋሪ አርሶአደር አለባቸው ደጄኔ እንዳሉት፣ ለሚያመርቱት የወተት ምርት መሸጫ ገበያ ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል።

አሁን በአካባቢው የሚገነባው ፋብሪካ የወተት ምርታቸውን በማቅረብ የተሻለ ዋጋ ተጠቃሚ ለመሆን ተስፋ እንዳሳደረባቸው ጠቁመዋል።

የፋብሪካው መገንባት ከወተት ምርታቸው የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ ለልጆቻቸውም ተጨማሪ የሥራ እድል ይፈጥራል የሚል ተሳፍ እንዳሳደረባቸው የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሞላ ደጄኔ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም